ምርቶችን በጥራት ለማቅረብ የተጀመረው የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አርሶ አደሮቻችን ያመረቱትን በጥራት ማቅረብ እንዲችሉ የተጀመረው የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ የወተት ማቀነባበሪያ በይፋ ስራ አስጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች እና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ መንግሥት ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ በትኩረት መስራቱ የሀገርን ብልጽግና ያረጋግጣል ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት የምርት አቅሙን በማዘመን እና በማስፋፋት ለረጅም ጊዜ የሚቆየውን ወተት ለገበያ ማቅረቡ በመላው ሀገሪቱ ወተት እንዲቀርብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ፋብሪካው ምንም እንኳ ዘመናዊ መሳሪያ የሚጠቀም ቢሆንም የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም ሚናው የጎላ እንደሆነ አንስተዋል።
አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፥ ግሩፑ ባለፉት ዓመታተት በተለያዩ ቴክኖሊጂዎች በመታገዝ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ ወተቶችን ሲያቀርብ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቀው ዘመናዊ የወተት ማቀነባበሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ወተቱ ያለ ማቀዝቀዣ ለስድስት ወራት የሚቆይ መሆኑን አብራርተዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ ወተት ወደ ክልሎች የሚደርስበት ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ከአርሶ አደሩ ይሰበሰብ የነበረውን የወተት ምርት ከፍ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
በቅድስት ብርሃኑ