Fana: At a Speed of Life!

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተኪ ምርቶችን በማምረት መፍትሔ እየሆኑ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማምረት መፍትሔ እየሆኑ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

16ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት “የቴክኖሎጂ ልህቀት ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ በአራዳ ፓርክ ተከፍቷል።

ከንቲባዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን በማውጣት ለሀገር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እያበረከቱ ይገኛሉ።

የሚሰሩ እጆችና የሚፈጥሩ አዕምሮዎች በሀገር ግንባታ ውስጥ የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልጸው÷ ሀገር ብዙ በምትፈልግበት ወቅት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተኪ ምርቶችን በማምረት መፍትሔ እየሆኑ ነው ብለዋል።

ውጤታማነታቸው እያደገ መምጣቱንም ጠቅሰው÷ ለውጭ ገበያ የሚበቁ ምርቶች እና የፈጠራ ውጤቶች እየሰፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህም በአዲስ አበባ የሚታዩ አዳዲስ የመንገድ መብራቶች ማሳያ ናቸው ነው ያሉት።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው÷ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኒክ ብቁ የሆነ ፈጣሪ ዜጋን ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

መንግሥትም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት 14 ኮሌጆችና 1 የልህቀት ማዕከል ተሳታፊ ሆነዋል።

በአሸብር ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.