Fana: At a Speed of Life!

የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በሶማሌ ክልል የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፥ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን መመረቃቸውንና አዳዲስ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡

የሶማሌ ክልል በፈጣን የእድገት ጉዞ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፥ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አስደናቂ ድሎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በክልሉ ሲቲ ዞን ሽንሌ ወረዳ ህብረተሰቡን በስፋት ሊጠቅሙ የሚችሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች በክልሉና በፌደራል መንግሥት ጥምረት እንዲሁም በግል ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋይ በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በማዕድን ኢንቨስትመንትና በስራ እድል ፈጠራ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች በተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም የዋቢ ግሩፕ የግራናይት ፋብሪካ የስራ እድልን ከመፍጠሩ በላይ የግራናይት ውጤቶችን በማምረት በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ችሏል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በሽንሌ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ፥ የኦክስጅን ግብዓቶችን ለሽንሌ፣ አይሻ፣ ቢኪ ሆስፒታሎችና በዞኑ ውስጥ ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ለድሬዳዋ አጎራባች አካባቢዎች ማቅረብ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በጉብኝታቸው ከድሬዳዋ ሽንሌ የተሰራውን የአስፋልት መንገድ የመረቁ ሲሆን፥ ወደ ጂቡቲ የሚሄደውን መንገድ ከመርማርሳ ከተማ የሚያገናኘውና በኮሪደር እሳቤ በክልሉ መንግሥት ወጪ ለሚሰራው የአስፋልት መንገድ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.