ኮፕ-32 ለኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት የተሰጠ እውቅና ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የኮፕ-32 ጉባኤን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው የአካባቢ ጥበቃ ጥረቷ አለም አቀፍ ዕውቅና ስላገኘ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ተክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና ዳር ድንበሯን አስከብራ የቆየች ሀገር መሆኗን አውስተው፤ የተፈጥሮ ሀብቷን ግን በተገቢው መልኩ ባለማልማቷ ለሌሎች ሀገራት መጠቀሚያ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተስፋ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠበቅ ነው በሚል እሳቤ በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸው ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዘንድሮው ዓመት ከ8 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለትም በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር ኢትዮጵያን አረንሻዴ ለማልበስ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እየተሳተፈ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ በተከናወኑ ስራዎች የኢትዮጵያን የአፈር ሀብት መመለስ፣ የደን ሽፋንን ማሳደግ እንዲሁም ጠፍተው የነበሩ ሀይቆችና የዱር እንስሳት መመለሳቸውን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከህግ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊና ከተቋማት ማሻሻያዎች በተጨማሪ በአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡
አፍሪካ በኢንዱስትሪ ያደጉ ሀገራት በሚያደርሱት የአየር ንብረት ተፅዕኖ በርካታ ጉዳቶች እየደረሱባት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አረንጓዴ ዐሻራ ይህንን ተፅዕኖ ለመከላከል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ