በመዲናዋ በቀዳማይ ልጅነት ላይ ለዓለም ተሞክሮ የሚሆን ሥራ ተከናውኗል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ ከተማ በቀዳማይ ልጅነት ላይ ለዓለም ተሞክሮ የሚሆን ሥራ ሰርታለች አሉ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ ማስጀመርያ መርሐ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሂዷል።
ከንቲባዋ በወቅቱ እንዳሉት ÷ አዲስ አበባ ህፃናትን ለማሳደግ ምቹ የአፍሪካ ከተማ እንድትሆን አስፈላጊ መሰረተ ልማት ተሰርቶ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።
እንደ አዲስ አበባ ከተማ “ህፃናት የአዲስ አበባ የነገ ተስፋዎች” በሚል መሪ ሐሳብ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ለሚሆኑ ከ6 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ሁለንተናዊ እድገት መረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከፅንስ ጀምሮ እስከ 6 ዓመት ዕድሜ ባሉ ህፃናት ላይ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ በትኩረት መሰራቱ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለማህበረሰቡ ብሎም ለሀገር ዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የመጀመሪያዎቹ 6 ዓመታት የሚሰሩ ሥራዎች በትምህርት፣ በሰው ሀብት ልማት እና በኢኮኖሚ እድገት ላይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያሳድሩ ጠቁመዋል።
ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ወደ 330 ሺህ ለሚጠጉ ቤተሰቦች የቤት ለቤት ጉብኝት የሚያደርጉ እና ለወላጆች ምክር የሚሰጡ ከ5 ሺህ በላይ የወላጅ ምክርና አቅም ግንባታ ባለሙያዎችን በማሰማራት አገልግሎቱን ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
መንግሥት የቀዳማይ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ ከማቅረብ ባሻገር የትምህርት ቁሳቁሶችና ዩኒፎርሞችን ከክፍያ ነጻ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
የተቀናጀ የቀዳማይ ልጅነት ልማት አገልግሎት በሁሉም የመንግሥት ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች በመደበኛነት እየተሰጠ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ከመኖሪያ ቤታቸው ርቀው በሥራ ላይ ለተሰማሩ ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ ቤተሰቦች አገልግሎት የሚሰጡ ከ1 ሺህ በላይ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት መቋቋማቸውን ገልጸው፤ በማዕከላቱ ከ7 ሺህ 700 በላይ ህፃናትን ለሚንከባከቡ ሞግዚቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ነው ያመለከቱት።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከ5 ሺህ በላይ የሚሆን የህጻናት መጫወቻዎች ተገንብተዋል ብለዋል።
በሲፈን መኮንን