Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ – አረንጓዴ ዐሻራ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለማችንን በአሁኑ ወቅት እየፈተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ጫናዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ሰጪ ርምጃ ጀምራ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

ከእነዚህ ተግባራት መካከል ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሆኗል።

በመንግሥት ቆራጥነት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያውያንን ልብና ጉልበት በአንድነት ያስተሳሰረ ታላቅ ሀገራዊ ተግባር ሆኖ ቀጥሏል።

ይህ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በይፋ የተጀመረው መርሐ ግብር ዛፍ ከመትከል ባሻገር የሀገሪቱን የተፈጥሮ ጤና የሚመልስና የተራቆቱ መሬቶችን ዳግም ለማለምለም የተወጠነ ግዙፍ ንቅናቄ በርካታ ውጤት አስመዝግቧል።

መንግሥት ለመርሐ ግብሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በባለቤትነት በመምራትና ህዝቡም ጥሪውን ተቀብሎ በነቂስ በመውጣት ላለፉት ዓመታት ያሳዩት ቁርጠኝነት የሀገሪቱን ደን ሽፋን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ብቻ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

በዚህም የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ ይህም ከቁጥር ባለፈ በተጨባጭ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለመጣው ለውጥ ማሳያ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ ይወድም የነበረው 72 ሺህ ሄክታር ደን ወደ 3 ሺህ ሄክታር ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

በወንዞች ላይ የሚፈጠረው ደለል እንዲቀንስ እና በወንዞች ላይ ይከማች የነበረው 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን ዓመታዊ የደለል ክምችት ወደ 208 ሚሊየን ቶን እንዲቀንስ በማድረግ ለውሃ ሀብት ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።

በተመሳሳይ መልኩ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ይደርስ የነበረው 130 ቶን ዓመታዊ የአፈር መሸርሸር አሁን ላይ ወደ 54 ቶን ዝቅ እንዲል በማስቻል ለምርታማነት እና ለአፈር ለምነት ትልቅ በረከት ሆኗል።

መርሐ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን፤ ለወጣቶችና ለሴቶች የገቢ ምንጭ በመሆን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የአረንጓዴ ስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ችግኞችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ በቤተሰብ ደረጃ ተጨማሪ ገቢና የምግብ ምንጭ መሆን ችሏል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን በመንግሥት ጥሪና በራሳቸው ፍላጎት ለምድራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር የገለጡበት መርሐ ግብሩ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

ኢትዮጵያውያን ዝናብ እና ፀሐይ ሳይበግራቸው ጉድጓድ በመቆፈር፣ ችግኝ በመትከል፣ የተተከሉትን በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ አረንጓዴና የተመቸች ሀገርን ለመገንባት ጠንካራ መሰረት በመጣል ላይ ናቸው።

አሁንም መንግሥት ቁርጠኝነቱን በማጠናከር እንዲሁም ሕዝቡ በየዓመቱ የሚያሳየውን የመተባበር ስሜት በማደስ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ተምሳሌት እንድትሆን መስራታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.