በምርጫው ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሀገር ማሸነፍ አለባቸው – የአማራ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምርጫው ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሀገር ማሸነፍ አለባቸው አለ የአማራ ክልል ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን ተከትሎ ፓርቲዎች ከመካሰስ እና ከመሳደድ በመውጣት አብሮ የመስራት ባሕልን ማዳበር መቻሉን አንስተዋል።
ችግሮች ሲያጋጥሙ በጋራ ምክር ቤት መድረክ እየተወያየን እየፈታን ዘልቀናል ያሉት አቶ ተስፋሁን÷ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚደረገው ዝግጅትም የእጩዎች እና የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ በሌሎች ተግባራት ላይ በመናበብ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የጋራ ምክር ቤቱንም በሐሳብ የመሟገት ባሕል ለማሳደግ ተጠቅመንበታልም ነው ያሉት።
ሕዝባችንም የሚበጀውን ለመምረጥ መወሰን የሚያስችል ዕድል አግኝቷል፤ በሂደቱ ጥሩ የዴሞክራሲ ልምምድ ተገኝቶበታል ሲሉም ገልጸዋል።
ሕዝቡ የመራጮችን ካርድ በማውጣት የሰላም ጥማቱን እና የዴሞክራሲ መራጭነቱን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ሕዝቡ በምዝገባ ያሳየውን ሰፊ ፍላጎት በድምፅ መስጫ ቀንም በመውጣት ድምጹን እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሀገር እንዲያሸንፉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።