Fana: At a Speed of Life!

የአሚ’ አ ከተማ ሞዛርት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እርሱ ከአያቱ እግር ስር ከእግር ኳስ ይልቅ የፈረንሳይን ስነ ጽሁፍና ፍልስፍና እየተጋተ በጥበባዊ ተረኮች ፍቅር ሲከንፍ፥ እኩዮቹ ግን ቅሪላ ሲለጉ ይውላሉ።

ለዛም ነው በፈረንጆቹ 1977 በአሚ’ አ ከተማ ከሀኪም ቤተሰቦች የተገኘው አዳጊ ፒያኖን ሲጫወት ልክ እንደ ሞዛርት ይሉት ውዳሴን እስከ ማግኘት አድርሶታል።

በከተማዋ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለአስር አመታት ያጠናው ፒያኖ ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር አስታግሶበታል።

ይህ የጥበብ ፍቅር ግን በትምህርቱ ላይ እንቅፋት አልሆነበትም። በፈረንሳይ ምርጥ የሚባሉትን የፖለቲካ ሳይንስ እና የመንግስት አስተዳደር ትምህርት ቤቶችን እና በታዋቂው የሊቃውንት ማፍሪያ ኤና ስልጠናውን ወስዷል።

ከፒያኖው ፊት ተቀምጦ ሙዚቃ እንደሚያቀናብር አርቲስት ፖለቲካንም በስልትና በድፍረት የሚመራ ሆኖ ለፈረንሳይ ፕሬዚዳንት እስከ መሆን የደረሰ ስኬቱ የሚጀምረው እንዲህ ነው።

ሙዚቀኛ ፣ የባንክ ዓለም ሰው ከዛም ፖለቲካኛው ኢማኑኤል ማክሮን።

የማክሮን የሙያ መስመር በሁለት ዓለማት መካከል የተወጠረ ነበር።

በመጀመሪያ በሮዝቺልድ የኢንቨስትመንት ባንክ ውስጥ ሲሰራ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሚሊየን ዩሮዎችን ያስገኘ ስምምነት በመፈጸም “ወርቃማው ልጅ” በሚል ቅጽል በምጣኔ ሀብት እውቀቱ ተወደሰ።

ይህ የኢኮኖሚ እውቀት ደግሞ ወደ ፖለቲካው ዓለም ደጃፍ ቀይ ምንጣፍ ሆኖ ተረማመደበት።

በፈረንጆቹ 2014 ስልጣን ላይ የነበሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንድ የኢኮኖሚ ሚኒስትር የሹመት ካባን ደረቡለት። ፒያኖ… ባንክ… ከዛም ፖለቲካ… በየምዕራፉ ተሸጋገራቸው።

ሆኖም ፒያኖን በራሱ ጣቶች የሚያዘው ወጣቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ማክሮን በሌሎች ጥላ ስር መታዘዝን አልፈቀደም።

ግራ ቀኝ የተወጠረውን የፈረንሳይ ፖለቲካ መጓተት በአዲስ የለውጥ ሀሳብ ሰንጥቆት ወጣ። ለዚህ የፈጀበት ሁለት አመት ብቻ ነበር።

“አን ማርሽ” የተሰኘው ንቅናቄ፥ አዲሱ ሀሳብ በአዲስ መንገድ በወጣቱ የፖለቲካ ሰው የፈረንሳይ የፖለቲካ ካርታን አዛብቶ ብቅ አለ።

በጉዞ ላይ አለ ያኔ፥ “ግራ ወይም ቀኝ አይደለሁም፤ ለፈረንሳይ ነኝ” በሚል መርህ ህዝቡን ቀሰቀሰ።

ፓርቲው በኋላ ላይ ሪናይሳንስ ፓርቲ ሆኗል።

በኋላም በ39 ዓመቱ በፈረንሳይ ታሪክ ወጣቱ ፕሬዚዳንት በመሆን የኤሊዜ ቤተመንግስትን ተቆጣጠረ።

እሳቸው ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በስልጣን ዘመናቸው የፈረንሳይን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ደፋር ርምጃዎችን መውሰዳቸው ይነገርላቸዋል።

ንግድን ያነቃቃው ፖሊሲያቸው እንዲሁም የጡረታ ማሻሻያዎች ይጠቀስላቸዋል።

በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው የአውሮፓ መሪ ለመሆን ጥረት የሚያደርጉት ፕሬዚዳንቱ የፓሪስን ተፅእኖ ፈጣሪነት የሚያሳድግ ስልትን ይከተላሉ።

አውሮፓ በምስራቅ አቅጣጫ ለተቃጣባት ጦርነት መፍትሄ ፍለጋን ባክነዋል፡፡

አውሮፓ የደህንነቷ ቁልፍ በራሷ እጅ እንዲሆን ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ ስለ አህጉሪቱ መጻኢ ጊዜ የሀያላን ሀገራት መሪዎችን የቃላት ጦርነት በተደጋጋሚ ተጋፍጠዋል።

አፍሪካ እና ፈረንሳይ እንደ ምድር ካርታ ርቀት ሳይሆን ጓዷዋ ድረስ ይተዋወቃሉ።

ይህን ቅርበት በጋራ ተጠቃሚነት ለነገ በአዲስ የዲፕሎማሲ ትወራ ለመሳል ጥረት ላይ እንደሚገኙም ይነገርላቸዋል።

በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ልዩ ትኩረት በመስጠት ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጠበቁና የኢኮኖሚ አጋርነት እንዲጠናከር በማድረግ ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ደጋግመው ጎብኝተዋታል።

ፓሪስ እና አዲስ አበባ ድሮ በምንዱባን ትረካ፣ በሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት እና የአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ትዝታ ብቻ ተጋምደው አልቀሩም፡፡

ዛሬም በአዳዲስ ትብብሮች ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ሊያስጠብቁ በመሪዎቻቸው አጋርነታቸውን አጥብቀዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በኃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.