Fana: At a Speed of Life!

ከተማችንን ለማበልጸግ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተማችንን ይበልጥ ለማበልጸግ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

የአዲስ አበባን እድገት እና የለውጥ ጉዞ የሚዘክረው እና አዲስ እንደ አዲስ የተሰኘው መጽሐፍ በዛሬው እለት በይፋ ተመርቋል፡፡

በመጽሐፉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች እና የመጽሐፉ ፀሀፊዎች ተገኝተዋል።

ከንቲባዋ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ መጽሐፉ ለህዝባችን ቃል ገብተን፣ ቃላችንን በተግባር የቀየርንበትን ታሪክ የሚተርክ ነው ብለዋል።

ውጤቱ ሕዝቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ በሀሳቡ የተሳተፈበት እንደሆነም ገልጸዋል።

እንግሊዛዊው ጸሐፊ ኘሮፌሰር ስሞን ሊ፣ ዶ/ር ክሌመንት ካቱሉሺ፣ ትዉልደ ኢትዮጵያዊው ዶ/ ር ሂርዾ ቁምቢ እና ቡድናቸው በጋራ ለጻፉት መጽሐፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ጠንካራ እሳቤ ወደ ተጨባጭ ስኬት መቀየሩን እና የአዲስ አበባን ትራንስፎርሜሽን ያሳየ እንዲሁም ለትውልድ የሚሻገር ታሪክን የሰነደ መጽሐፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

የባህር ማዶ ሰዎችን ቀልብ በሳበው የከተማችን ልማት፤ የሺዎች ድካምና ብርታት፣ የትውልድ አሻራ ለማሳረፍ የደከሙትን ሁሉ እውቅና እንሰጣለን፤ እናመሰግናለን ነው ያሉት።

የለውጥ ጉዞው የሁላችንም ኩራት ሲሆን፣ በቀጣይም ከተማችንን ይበልጥ ለማበልጸግ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በቅድስት ብርሀኑ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.