Fana: At a Speed of Life!

በክልሎቹ ትብብር የሕዝቡን የጋራ ሰላምና ልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ትብብር የሕዝቡን የጋራ ሰላምና ልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ውጤት እያመጡ ናቸው።

በአሶሳ ከተማ የተገነባው የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ ክልሎች የጋራ ሰላምና የልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሕንጻ ተመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ እና የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ተገኝተዋል።

አቶ አሻድሊ ሐሰን በወቅቱ እንደተናገሩት÷ ሦስቱ ክልሎች በጋራ እያከናወኗቸው የሚገኙት የሰላምና የልማት ሥራዎች በክልሎቹ መካከል ትብብር እንዲጎለብት አድርገዋል።

የሕንጻው ግንባታ በክልሎቹ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የሦስቱ ክልሎች የሰላምና የልማት ትብብር የመደመር አስተሳሰብን በተግባር የሚያሳይ እና የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ በሦስቱ ክልሎች መካከል እየተገነባ ያለው የመሠረተ ልማት እና የሰላም ጥበቃ ስራ የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነትን ይበልጥ እያጠናከረ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በተለይም የጋራ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሰላም እሴት ግንባታና በሕዝባዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ይህም በሦስቱ ክልሎች መካከል ለሚኖረው ጠንካራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አስተማማኝ መሠረት መጣሉን ጠቅሰዋል።

ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) የሦስቱ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በክልሎቹ መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።

በአሶሳ ከተማ የተገነባው የሦስቱ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለ አራት ወለል ሕንጻ ሲሆን÷ ለግንባታው 300 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.