የአዋሽ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 467 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዋሽ ባንክ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋፋት ባደረገው ጥረት ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡን 467 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አድርሷል።
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንዳሉት፤ አዋሽ ባንክ በ2025/26 በጀት ዓመት አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል።
በበጀት ዓመቱ ከ17 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ገልጸው፤ የሕብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማዳበርና የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 467 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡
የዘንድሮ ተቀማጭ ገንዘብ ከአምናው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ41 በመቶ ወይም የ135 ቢሊየን ብር ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል።
ይህም ጭማሪ በአዋሽ ባንክ ታሪክ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተመዘገበ እጅግ ከፍተኛው የተቀማጭ ገንዘብ እድገት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተመሣሣይ መልኩ የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መንግሥት ባደረገው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ፖሊሲ እና ባንኩ በወሰዳቸው የአሠራርና የፖሊሲ ማሻሻያ ርምጃዎች የተነሣ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን አብራርተዋል።
ከተለያዩ ምንጮች ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ከአምናው ተመሣሣይ ወቅት አንጻር የ635 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ በማሣየት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር ሆኗል ብለዋል።
ባንኩ የህብረተሰቡን የብድር አገልግሎት ለማርካት በአዋሽ ለሁሉም፣ በጥላ እና በእርፍ የዲጂታል አማራጭ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ በማበደር ከ1 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ አድርጓል።
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 622 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን የተከፈለ ካፒታሉ ዘንድሮ የ10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማስመዝገብ 38 ነጥብ 5 ቢሊየን ደርሷል።
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች ሊኖራቸው ይገባል ብሎ ካስቀመጠው ዝቅተኛው የ5 ቢሊየን ብር ከሰባት እጥፍ በላይ መሆኑ የተለያዩ ስጋቶችን የመቋቋም አቅሙ እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የበጀት ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 85 ነጥብ 37 ቢሊየን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፤ 40 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ ለተለያዩ ችግሮች ለተጋለጡ የህብረተሰቡ ክፍሎች 500 ሚሊየን ብር ያህል ወጪ በማድረግ ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱ ተገልጿል፡፡
በመቅደስ ከበደ