ሱዳንን ከኢትዮጵያ ጋር የማጋጨት ሙከራ የሱዳናውያን ሳይሆን የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ነው – ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰሞኑን የተስተዋለው ሱዳንን ከኢትዮጵያ ጋር የማጋጨት ሙከራ የሱዳናውያን ሳይሆን የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ነው አለች ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ ራሻ አዋድ፡፡
ጋዜጠኛዋ ከፋና አረብኛ ፖድካስት ጋር ባደረገችው ቆይታ፥ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት በልማትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጻለች፡፡
በቅርቡ ከሱዳን የጦር ኃይሎች በኩል በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን በመግለጽ፥ የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም የማይወክል የግብጽና ሌሎች የውጭ ኃይሎች አጀንዳ ነው ብላለች፡፡
በተለይም ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ግጭት ለማስገባት ሙከራ እንደምታደርግም ነው የገለጸችው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ቀጣናዊ ውጥረቶች እየተሸጋገረ የሚገኘውን የሱዳን ጦርነት ለማስቆም መፍትሄው ከውስጥ ሊጀምር እንደሚገባ አስገንዝባለች፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ውጥረት የመፍጠር ዘመቻ ከሱዳን ብሔራዊ ጥቅም ጋር የማይገናኝ ነው ያለችው ጋዜጠኛዋ፥ ሱዳን “ከግብፅ ጣልቃ ገብነት” ራሷን ማራቅ እንዳለባት ተናግራለች፡፡
ሱዳን በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የግብጽን አቋም እንድትቀበል የሚያደርግ ግንኙነት እንደነበራት በማስታወስ፥ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስቀድም ገለልተኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መገንባት እንዳለባት አስገንዝባለች፡፡
አንዳንድ የሱዳን ጦር ኃይል መሪዎች ከተጠያቂነትን ለማምለጥ ቀውሱን ወደ ውጭ ለመግፋት እየሞከሩ ነው ያለችው ራሻ አዋድ፥ ከኃይል እንቅስቃሴ ይልቅ ውይይትና ዲፕሎማሲን እንዲመርጡ ጠይቃለች።
በአህመድ አብዱልባር