Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ መስፈን ያላት ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ መስፈን ያላት ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) ከአዲሱ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ዳይሬክተር ብ/ጄነራል ሮናልድ ርዊቫንጋ እና ከተሰናባቹ ዳይሬክተር ብ/ጄነራል ፖል ካሁሪያ ንጄማ ጋር ተወያይተዋል።

የቀድሞው ዳይሬክተር የተጠንቀቅ ኃይሉ ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳይ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ የቀጣናውን የሰላምና ደህንነት ተግዳሮት ለመፍታት ላሳየችው ቁርጠኝነትና የመሪነት ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተጠንቀቅ ኃይሉ የተመሰረተው የአባል ሀገራትን ጥምረትና ፖለቲካዊ አንድነት ለማሳደግ መሆኑን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ ለተጠንቀቅ ኃይሉ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም እና ፀጥታ መስፈን ያበረከተችውና እያበረከተችው የምትገኘው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አውስተው፥ ይህንን ሚናዋን በአግባቡ መወጣቷን ትቀጥላለች ነው ያሉት።

አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው ያሉ የሰላምና የደህንነት ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰው፥ በቀጣይም ይህንን ድጋፏን ከአጋር አካላት ጋር በተናበበ መልኩ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

አዲሱ ዳይሬክተር ብ/ጄኔራል ሮናልድ ርዊቫንጋ ኢትዮጵያ የቀደመውን ጉልህ ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል እምነታቸውን ገልጸው፥ በትብብር እንደሚሰሩ መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.