ከሆርቲካልቸር ምርቶች ወጪ ንግድ ከ400 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 10 ወራት 236 ሺህ 415 ቶን የሆርቲካልቸር ምርት ወደ ውጭ በመላክ 408 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል አሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ።
ሚኒስትሩ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጊዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የሙዝ ክላስተርና የሎሚ ምርት እንዲሁም በባቱ ከተማ የአበባ ምርትን ጎብኝተዋል።
አቶ አዲሱ በዚህ ወቅት ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ በዚህ ዓመት ከዘርፉ ወጪ ንግድ 600 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ባለፉት 10 ወራት 408 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል።
በአትክልትና ፍራፍሬ በተለይም በአቮካዶ ምርት ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ተቋቁሞ ምርቱን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ እያደገ የመጣውን የዜጎችን የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የግብርና ምርቶችን ለሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች ለጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ከንዑስ ዘርፉ ለሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
የግብርናው ዘርፍ 10 ዓመት መሪ ዕቅድ መሰረት በትኩረት ከሚሰራባቸው ንዑስ ዘርፎች መካከል አንዱ የሆርቲካልቸር ልማት መሆኑም በዚህ ወቅት ተገልጿል፡፡
በፌናን ንጉሴ