በምርጫ ካርዳችን ለፈለግነው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ዝግጁ ነን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በወሰድነው ምርጫ ካርድ ለፈለግነው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ዝግጁ ነን አሉ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የወላይታ ዞን ነዋሪዎች፡፡
ነዋሪዎቹ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የወሰዱትን የምርጫ ካርድ ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም የወሰዱትን የምርጫ ካርድ ለሚፈልጉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡
ካርድ ወስዶ ሳይመርጡ መቅረት የራስን መብት ለሌላው አሳልፎ ከመስጠት እንደማይተናነስ አብራርተዋል፡፡
ስለሆነም ዜጎች የወሰዱት ምርጫ ካርድ ትልቅ ዋጋ እንዳለው በመገንዘብ ለልማትና ለሀገር እድገት ይሆናል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ሊጠቀሙበት ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሕዝብ ነጻ ምርጫ የሚመጣ መንግሥት የሕዝብን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት እንደሚሠራና አደራውንም እንደሚወጣ አመልክተዋል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚከናወነው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች የወሰዱትን የምርጫ ካርድ በአግባቡ በመጠቀም የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም ነዋሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በታሪክነሽ ሴታ