ዩናይትድ ኪንግደም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከ20 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩናይትድ ኪንግደም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከ20 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርጋለች፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ፣ የጋራ ብልጽግና እና ልማት ቢሮ ያደረገው ድጋፍ የማኅበሩን የሰብአዊ ምላሽ አቅምና የሚያከናውናቸውን ሥራዎች እንደሚያጠናክር ተገልጿል፡፡
በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች እንዲሁም የቀይ መስቀል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ድጋፉ ችግሮች በሚከስቱባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ተደራሽ ለመሆን የሚያስችል ነው፡፡
በተለይም ለጤናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፥ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ በበኩላቸው፥ የተደረገው ድጋፍ በተለይም ማኅበሩ ከዚህ ቀደም ከተሽከርካሪ ጋር ተያይዞ ይገጥመው የነበረውን ተግዳሮት የሚያስቀር እንደሆነ አብራርተዋል።
በዚህም ለሰብአዊ ምላሽና የውሃ አቅርቦት ስራዎች የሚውሉ 12 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ 10 የፍጥነት ተሽከርካሪዎች፣ ሦስት የውሃ ማጓጓዣ እንዲሁም አንድ የውሃ መቆፈሪያ፣ የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃ እና ክሬን ርክክብ ተደርጓል።
በቅድስት ብርሃኑ