7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እያደረገ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ለፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ማብራሪያ ሰጥቷል።
በዚሁ ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ለምርጫው ያደረገው ዝግጅት እጅግ ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ ቢሆንም መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎች እነዚህን የጥፋት ዕቅዶች ማክሸፉን አረጋግጠዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና በተለይም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው÷ የጋራ ግብረ ኃይሉ ከምርጫ ቦርድ ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥና ከሕዝቡ ጋር በመተባበር እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በቅድመ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት ደህንነት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን አንስተዋል።
በሳራ ስዩም