7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታችና አሳታፊ ነበር – ኡሁሩ ኬንያታ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታችና አሳታፊ ነበር አሉ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች መሪ እና የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፡፡
ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያ ያካሄደችውን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ምርጫው አካታችና አሳታፊ እንዲሆን መንግስት ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን የቅደመ ምርጫ ክንውኖችንና የምርጫ ዝግጅቶችን በተመለከተ ቅኝት ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ከምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች፣ ከመንግስት ተቋማት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከተለያዩ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በደምፅ መስጫው ዕለት የምርጫ አስፈጻሚዎች መራጮችን በአግባቡ ማስተባበራቸውን ጠቅሰው፥ የጸጥታ አካላት ገለልተኝነታቸውን በጠበቀ መልኩ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ማስፈጸማቸውን አብራርተዋል፡፡
ሕዝቡ ረጃጅም ሰልፎችን በመጠበቅ በትዕግስት ሲመርጥ እንደነበር ገልጸው፥ ኹነቱን የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምርጫው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አካታችና አሳታፊ ምርጫ ለማድረግ ያደረገውን ጥረት በማድነቅ፤ በሀገሪቱ ብዝሃነትን ለማረጋገጥና እኩል የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲሰፍን ለማድረግ ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኅብረቱ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር የሚያደርገውን ድጋፍ እና ምክረ ሀሳብ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ