Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳያጋጥም በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ለ2018/19 መኸር እርሻ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳያጋጥም በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻው እንዳሉት÷ በክልሉ በተያዘው የምርት ዘመን 5 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት በማረስ ከ205 ሚሊየን በላይ ኩንታል ሰብል ለማምረት ታቅዷል።

ዕቅዱን ለማሳካት የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ለማስገባት መታቀዱን ጠቁመዋል።

ከዚህም ውስጥ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የሚሆነው የክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ዕቅድ ወደብ ላይ መድረሱን አንስተው÷ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ወደ ክልሉ ተጓጉዞ ደርሷል ብለዋል።

ከባለፈው ዓመት የተረፈ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት መኖሩንና እስካሁን 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደርች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም እንዳለውና ለስርጭት የቀረበው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ቀድመው ከሚዘሩ ሰብሎች አኳያ በጥሩ የሚታይ እንደሆነም አንስተዋል።

በሌላ በኩል 220 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን ባለው ጊዜ 208 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ድልድል ተደርጓል ማለታቸውን የዘገበው አሚኮ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.