የመዲናዋ የወንዞች ዳርቻ ልማት፤ የወንዝ ዳርቻዎችን ከማስዋብ ያለፈ ፋይዳን የያዘ ፕሮጀክት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት፤ የወንዝ ዳርቻዎችን ከማስዋብ ያለፈ ፋይዳን የያዘ ፕሮጀክት ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ልዩ የሚያደርገው ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው ነው ብለዋል።
ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ እንዲሁም ከእንጦጦ እስከ ቀበና ባለው መስመር የሚከናወነው መጠነ ሰፊ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ከወንዞቹ ባሻገር እስከ 50 ሜትር የሚዘልቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የአረንጓዴ ኮሪደሮችን፣ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን እና የንግድ ቦታዎችን ልማት ያካተተ ሲሆን÷ ከተማዋንም በእጅጉ የቀየረ እንደሆነ አብራርተዋል።
የወንዝ ዳርቻዎችን ገጽታ እና አገልግሎት ከማሻሻል ባለፈ በኮንስትራክሽን፣ በኢንጂነሪንግ፣ በመልክዓ ምድር ውበት ግንባታ፣ በሎጂስቲክስ እና በተያያዙ ዘርፎች ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠቁን ጠቅሰዋል፡፡
ለሀገር በቀል ተቋራጮች፣ አቅራቢዎች እና ንግዶችም ዕድሎችን አመቻችቷል ነው ያሉት።
አብዛኛው ሥራ በሀገር ውስጥ መሐንዲሶች መቀረጹና መተግበሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በከተማ ልማት እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ያላቸው አቅም እያደገ መምጣቱን ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።
የልማቱ ዘላቂነትም እኩል ትኩረት የሚሰጠው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ቀደም ሲል መርዛማ ኬሚካሎች እና ቆሻሻዎች የሚጣሉባቸው፣ በወንዝ ዳርቻዎች በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ የጎርፍ አደጋ ይጋርጡ የነበሩት እነዚህ አካባቢዎች አሁን ወደ አረንጓዴ፣ ጤናማና ለሕይወት ምቹ ወደሆነ የከተማ ቦታነት እየተቀየሩ ይገኛል ብለዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም የንግድ እና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ተቀናጅተው መገንባታቸው የአካባቢ ጥበቃ እና የኢኮኖሚ ዕድገት ከዚህ ቀደም ከነበረው ያልተናበበ ስራ ተላቀው በጥናትና በጋራ ግብ ተባብሮ መስራት እንደሚችሉ ማረጋገጫ መሆኑንም አመልክተዋል።
ይህ ፈጣን የልማት ሥራ አዲስ አበባን አረንጓዴ፣ ይበልጥ የተሳሰረች፣ በኢኮኖሚ ንቁ እና ሰውን ማዕከል ያደረገች ከተማ የማድረግ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ላይ መሰረት የተጣለበት የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡