ምርጫውን ለማደናቀፍ የውስጥም የውጭም ጽንፈኞች ያቀዱትን ሴራ ማክሸፍ ተችሏል – የሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ የውስጥም የውጭም ጽንፈኞች ያቀዱትን ሴራ ማክሸፍ ተችሏል አለ የሰላም ሚኒስቴር፡፡
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ በሰጡት መግለጫ በምርጫው ዕለት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ድምጽ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫውን የሕልውናና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማረጋገጫ አድርጎ በመውሰድ በቅንጅት መስራቱን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተካሄደውን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍና የሕዝብን ሰላም ለማደፍረስ ጽንፈኛ ኃይሎች የከፈቱት ሁለንተናዊ ጥቃት መክሸፉን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፅንፈኝነትን በመቃወም ሀገርን የሚያስቀጥል ሕጋዊ መንግሥት ለመመስረት ያለውን ጽኑ ፍላጎት አሳይቷል ብለዋል፡፡
አፍራሽ ኃይሎቹ የመንግሥትን ሕጋዊ ቅቡልነት ለማሳጣትና ኢትዮጵያን ወደ ሥርዓት አልበኝነት ለመክተት ሕዝቡ የምርጫ ካርድ እንዳይወስድና በምርጫው ቀን ድምጽ እንዳይሰጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽንፈኝነትን አጀንዳ ውድቅ በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ተሳትፎ የምርጫ ካርድ በመውሰድ፣ በሰልፎች ላይ በነጻነት በመገኘትና በምርጫው ቀን በነቂስ ወጥቶ ድምጽ በመስጠት አፍራሽ ኃይሎችን ማሸነፉን ጠቁመዋል፡፡
የጸጥታ ተቋማት ባከናወኑት ወቅቱን የጠበቀና የተቀናጀ የጸጥታና ደህንነት ሥራ የሽብር ዕቅዶቹ ሊከሽፉ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡