በዲጂታሉ ዓለም የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ ብሔራዊ ርዕያችንን የምናፋጥንበት መነሻ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን የ5 ሚሊየን ኮደሮች ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
የ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮች ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰው፥ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ ሶፍትዌር ልማትና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም 5 ሚሊየን 5ሺህ 146 ሰልጣኞች መመዝገባቸውን ገልጸው፥ ከእነዚህም ውስጥ ከ3 ሚሊየን በላይ ሰልጣኞች ስልጠናውን አጠናቅቀዋል ነው ያሉት።
ይህ ስኬት የሕዝባችንን ቁርጠኝነት እና ወሰን የሌለው አቅም ማረጋገጫ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም. ድረስ የሰልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊየን ለማድረስ የተሰነቀውን ግብ ለማሳካት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ ብሔራዊ ተልዕኮ አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለወጣት ተማሪዎቻችን መጭው የክረምት ወቅት ትልቅ ዕድላችሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ የክረምት ወቅት ስልጠናውን በመውሰድ ተማሪዎች ብቻ ሳትሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላችሁ የዲጂታል መሪዎች እንድትሆኑ አሳስባለሁ ነው ያሉት።
ሥልጠናዎቹ ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚሰጡ ሲሆን የምስክር ወረቀቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡