Fana: At a Speed of Life!

ድንበሮች ለቀጣናዊ ውህደት ድልድይ ሆነው ሊያገለግሉ ይገባል – ቀነአ ያደታ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ድንበሮች ለቀጣናዊ ውህደት እንደ ድልድይ ሆነው ሊያገለግሉ ይገባል አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴዔታ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር)።

የኢትዮጵያን የድንበር አስተዳደር ለማጠናከርና ድንበሮችን የልማትና የሰላም ቀጣና ለማድረግ ያለመ ብሔራዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።

ቀነአ ያደታ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የሀገር ውስጥ ጥረቶችን ከአፍሪካ ሕብረት የድንበር አስተዳደር ስትራቴጂና ከአጀንዳ 2063 ጋር በማጣጣም ድንበሮችን የትብብርና የብልጽግና ቀጣናዎች ማድረግ ይገባል።

ድንበሮችን በድንበርነት ብቻ ከማየት ወጥቶ የደህንነት፣ የልማትና የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት የሚካሄድባቸው መሆናቸውን መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ድንበሮች ከፀጥታ ስጋቶችና ከሕገ ወጥ ተግባራት የሚከላከሉ የደህንነት መከታዎች መሆን እንዳለባቸው ገልጸው፥ ለቀጣናዊ ውህደት ድልድይ ሆነው ሊያገለግሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፥ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ መረጋጋት ለመፍጠር ዋና ከተሞች ብቻ ሳይሆኑ የድንበር አካባቢዎችና ማህበረሰቦች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ድንበሮችን ከፋፋይ አጥር አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ንቁ የንግድ ልውውጥና የህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚደረግባቸው እንዲሁም የታሪክ ውህደት የሚታይባቸው ቀጣናዎች ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ድንበሮች አሁንም ለፀጥታ ስጋቶችና ለኮንትሮባንድ ተጋላጭ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በተቃራኒው ለቀጣናዊ ትስስርና ለልማት ያላቸው ያልተነካ አቅም ሰፊ መሆኑ ተመላክቷል።

ይህንን ለማሻሻል ኢንስቲትዩቱ ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር በ12 የድንበር አካባቢዎች ላይ የመስክ ምልከታ በማድረግ ጭምር ያዘጋጀው ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ በጉባኤው ቀርቦ እንደሚጸድቅ ተመላክቷል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.