ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በመጪው ሐምሌ 8 ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳል አለ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡
ኮሚሽኑ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በ12 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ መሰብሰቡን ገልጸው፥ የምክክር ሂደቱ ግልፅነት በተሞላበት ሁኔታ መካሄዱን አንስተዋል።
በሀገሪቱ ያለው የችግር ቋጠሮ ሊፈታ የሚችለው በንግግርና ምክክር ብቻ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ሀገራዊ ምክክሩ አሁን ላይ ወደ ዋናው ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከሐምሌ 8 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፥ ተሳታፊዎች ጉባኤው ከመካሄዱ አንድ ሳምንት አስቀድመው ተጠቃለው አዲስ አበባ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
ተሳታፊዎች አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው እንዲጠብቁ ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ፥ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአለምሰገድ አሳዬ