በሀገራዊ ጉባኤው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ጽኑ መሰረት እንጥላለን – ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በመሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር ለዘላቂ ሰላም ጽኑ መሰረት የሚጣልበት ነው አሉ ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የምክክር ሒደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በጽናት በማለፍ ወደ ዋናውና ወሳኙ የምክክር ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ ቀጣይ ተግባራት በጉባኤው ላይ በኢትዮጵያ መሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ መነጋገርና ዘላቂ መግባባት ላይ መድረስ እንደሆነ አንስተዋል።
ውጤቱም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻልና መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲገነባ ያደርጋል ነው ያሉት።
ጉባኤው ለዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ ውስጣዊ ችግሮች ተፈተው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሰረት የሚጣልበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተከባብረው፣ ተነጋግረውና ተደማምጠው በመግባባት የሚያቀርቧቸው ምክረ ሃሳቦች በተግባር ተተርጉመው ሀገራችን ወደ አዲስ የሰላምና የእድገት ምዕራፍ እንድትሸጋገር የጋራ ቁርጠኝነትና ጥረት ይጠበቃል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም ለጉባኤው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ምክክር ተግባራትን ለማከናወን እንዲቻል የጉባኤው ተሳታፊዎች ጉባኤው ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ተጠቃልለው እንዲገቡ እንደሚደረግ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
በብርሃኑ አበራ