በኦሮሚያ ክልል የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ አካላት አጀንዳቸውን ለኮሚሽኑ አስረከቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማሕበረሰቡ የተቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል።
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች የቀድሞ ታጣቂዎችን የማወያየት ስራ ሲሰራ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በትናንትናው ዕለትም በኦሮሚያ ክልል የሰላም ጥሪውን ከተቀበሉ አካላት ውይይት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በቀድሞ ታጣቂዎቹ ፅኑ ፍላጎት መሆኑም ተመላክቷል።
በመድረኩ ላይ አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ ያስረከቡት እነዚህ አካላት ሌሎች ታጣቂዎችም ሰላማዊውን መንገድ እንዲከተሉ ምሳሌ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ እንዳሉት፥ ውይይቱ የምክክር ኮሚሽኑ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚመጡ አጀንዳዎችን ለመቀበል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ከሐምሌ 8 /2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአሸናፊ ሽብሩ