በትራፊክ አደጋ የ4 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከወላይታ ሶዶ ወደ ገሳ ከተማ ሲጓዝ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከሪካሪ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል።
አደጋው ልዩ ስሙ “ዛሮ ቁልቁለት” ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከሪካሪው በመገልበጡ ነው የደረሰው፡፡
በአደጋው እስካሁን የ4 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የገሳ ከተማ ፖሊስ የትራፊክ አደጋ መከላከል ቁጥጥር የሥራ ሒደት አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር አረጋ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሌሎች ተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቁመው ÷ ተጎጂዎቹ አቅራቢያ በሚገኝ ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ቦታው ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ እንደሚከሰትበት የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተሩ ÷ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡