መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ነው አለ የሐረሪ ክልል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን እንደገለጸው በሐረሪ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን አሳድጓል፡፡
ዘጠኝ ቁልፍ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ተቋማት በአንድ ጣሪያ ስር መሰባሰባቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገሩ ነው የተገለጸው፡፡
መንግሥት ለዜጎቹ የሚያቀርባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጥራት፣ ፍጥነትና ፍትሃዊነት የሀገርን ፖለቲካዊ መረጋጋትና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚበይኑ መጋቢዎች መሆናቸውን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡
የመደመር መንግሥት ዕሳቤ፤ በተቋማት ግንባታና አገልግሎት ጥራት በመደመር ፍልስፍና ውስጥ ጠንካራ የመንግሥት ተቋማትን መገንባት ለሀገር ግንባታ የጀርባ አጥንት እንደሚሆኑ ይገልጻል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግለሰባዊ ንክኪን በመቀነስና አሰራርን በቴክኖሎጂ በመተካት ተቋማት ከግለሰቦች መልካም ፈቃድ ይልቅ በሥርዓት ወደሚመራ ተቋማዊ ብቃት መሸጋገርን የሚያሳይ መሆኑን አንስቷል።
በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስር በአጠቃላይ 96 አገልግሎቶች ለህብረተሰብ በተቀላጠፈ መልኩ እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡
በማዕከሉ ዜጎች ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን በመቆጠብ እንግልትን ከማስቀረት ባሻገር ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ዜጎች ምቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተገልጋዮች ዘንድ እፎይታን መፍጠሩን የጽ/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ይህ ታላቅ ተግባርም ኢትዮጵያ በመደመር ዕሳቤ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥንና ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን አመኔታ በጽኑ መሠረት ላይ የሚገነባ ነው፡፡