Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቶች…

እንደ ዓድዋው ጦርነትና የድል ብስራት፤ እንደ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ርብርብና ብርሃን ሁሉ፣ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያሰለፈ ሀገራዊ ትልም ነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፡፡
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በፈረንጆቹ 2016 ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ በዓመት 92 ሺህ ሄክታር ደን በየዓመቱ ይጨፈጨፍ ነበር፡፡
በፈረንጆቹ 1900 የደን ሽፋናችን 40 በመቶ ከነበረበት ወደ ሦስት በመቶ ወርዶ ነበር፡፡
በተያያዥ የአፈር መሸርሸር ላይ በተደረገ ጥናት ቦሮቦራማ መልክዓ ምድር መገለጫችን ሆኖ፣ በሄክታር 130 ቶን አፈር ከእርሻ ማሳ ታጥቦ ይወሰድ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ጠቅላላው ከኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች 2 ቢሊየን ቶን አፈር ታጥቦ ይሄድ እንደነበር ነው ጥናቶች የሚያሳዩት፡፡
አካባቢያችንን በሥርዓቱ መንከባከብ ባለመቻላችን ድርቅና የምርታማነት መቀነስ፣ ጎርፍ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ የእንስሳት እልቂት እና የመሬት መንሸራተት ደጋግሞ ጉዳት አድርሶብናል፡፡
የብዝሃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት መራቆት እና የምርታማነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት በደለል መሞላትና የመጠን መቀነስ እንዲሁም መጥፋት ማህበረሰባችንን ለከፋ ድርቅ፣ ለጎርፍና ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡
ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) የሀሳብ አመንጭነት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተጀመረ፡፡
ከዚያን ዓመት ጀምሮ እንደ ሀገራዊ ንቅናቄ በመያዝ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የመትከልና የመንከባከብ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በ2011 ዓ.ም 40 ዛፎችን በነፍስ ወከፍ በሚል መሪ ቃል 4.7 ቢሊየን፣ በ2012 እየተጠነቀቅን እንትከል በሚል 5.9 ቢሊየን፣ 2013 ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል 6.8 ቢሊየን፣ በ2014 ዐሻራችን ለትውልዳችን በሚል 7.2 ቢሊየን፣2015 ነገን ዛሬ እንትከል በሚል 7.5 ቢሊየን፣ በ2016 የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ በሚል 7.5 ቢሊየን፣ 2017 በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል 8 ቢሊየን ችግኝ ተተክሏል፡፡
በሰባቱ ዓመታት 48 ቢሊየን ችግኝ የተተከለ ሲሆን÷ ችግኞቹም የጥምር የእርሻ ደንን 60 በመቶ፣ የደን ዛፍን 35 በመቶ እና የከተማ ውበት ዛፎች አምስት በመቶ ይይዛሉ፡፡
በ2010 ዓ.ም 17.2 በመቶ የነበረው የደን ሽፋናችን በ2016 ዓ.ም 23.6 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ የአረንጓዴነት ምጣኔን በአዋሽ ተፋሰስ እና በዓባይ ተፋሰስ ማሳደግ የተቻለ ሲሆን÷ በዚህም የውኃ አካላት መመለስና ማንሠራራት ጀምረዋል፡፡
በሰባቱ ዓመታት በአማካይ 25 ሚሊየን ሕዝብ የተሳተፈ ሲሆን÷ አንድ ችግኝ በአንድ ዶላር ቢሰላ በአጠቃላይ በሕብረተሰብ ተሳትፎ 48 ቢሊየን ዶላር አስተዋጽኦ ተደርጓል፡፡
በዚህ ሒደት የችግኝ ጣቢያዎች ብዛት ከ45 ሺህ ወደ 120 ሺህ አድጓል፤ 60 በመቶው የግል ነው፤እስካሁን በተከላ የተሸፈነው መሬት 11.2 ሚሊየን ሄክታር ነው፡፡
በዘንድሮው የ2018 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ደግሞ ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሃሳብ 8.5 ቢሊየን ለመትከል ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡
በአጠቃላይ በአንደኛው እና በ2ኛው ምዕራፍ የተተከሉ ችግኞችን 56 ቢሊየን ለማድርስ ግብ የታጣለ ሲሆን÷ ይህም ተግባር ሀገራችን በዓለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሐ ግብር የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡
ሥራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት አግሪኮላን እና የአውትስታንዲንግ አፍሪካን ሊደርሺፕ ሽልማቶችን እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል፡፡
በዚሁ የተነሳ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔና ሁለተኛውን የተባበሩት መንግሥታት የሥርዓተ ምግብ ጉባዔ ለማስተናገድ እድል አግኝታለች፡፡
በተጨማሪም 80ኛውን የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ጉባዔ ለዘላቂ ደን ልማት የተሰጠውን እውቅና እና ኮፕ32ን ለማስተናገድ እንድትታጭ አድርጓታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.