Fana: At a Speed of Life!

ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሰጠው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፈጣን እና ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ የአንድ ሀገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬት የሚለካው ከሩቅ ወዳጆቿ ይልቅ ከቅርብ ጎረቤቶቿ ጋር ባላት ትስስር ነው።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የመስጠት የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ደግሞ የዚሁ ማሳያ ነው።

በዚህም የኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውኅደት መፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለዓለም አቀፍ ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ፣ የኃያላን ሀገራት ፍትጊያ ማዕከልና ያልተነኩ ሃብቶች ወዳሏቸው የአፍሪካ ሀገራት ዋና መግቢያ በር ሆኖ ያገለግላል።

የአፍሪካ ቀንድ ዓለም አቀፍ ፍላጎትና ተግዳሮት የሚንፀባረቅበት ስትራቲጂካዊ ቀጣናም ሲሆን÷ ለአብነትም አሜሪካ፣ ቻይና፣ የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ የባሕረ ሰላጤ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የትኩረት ማዕከላቸው አድርገው ይመለከቱታል።

ኢትዮጵያም ቅድሚያ ለጎረቤት በሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በኢኮኖሚ ትስስር እንዲሁም በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች።

ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባሻገርም የተጋመደውን የቀጣናው ሕዝብ በኃይል እና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ለቀጣናዊና አሕጉራዊ የንግድ ስምምነት ትግበራ መሪ ሚናዋን እየተወጣች ነው።

በትራንስፖርትና በዲጂታል መሰረተ ልማት፣ በወደብና የባሕር በር አማራጭ የማስፋት ስራ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ውጤታማ አካሄድ መሆኑን በመረዳትም ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ናት።

የምስራቅ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱ አልሸባብን የመሳሰሉ የሽብርተኛ ቡድኖችን ህልም በማምከን የምታበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦም ለሁለትዮሽና ባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ውጤታማነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው።

የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በባሕል የጋራ ዕሴቶች የተጋመዱ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።

ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የልማት ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን ጥረት እያደረገችም ትገኛለች፡፡

ይህም የምትከተለውን የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ እና ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት የሰጠ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በቀጣይም ሀገራችን የጀመረችውን የምስራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት በማፋጠን፣ የውስጥና ቀጣናዊ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን በማስከበር ብሔራዊ ጥቅሟንና ፍላጎቷን የማረጋገጥ ሥራዋን ማጠናከር ይገባል፡፡

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.