ኮሚሽኑ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በመመከት በነጻነት ሥራውን እየከወነ ነው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የውስጥና የውጭ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በመመከት በነጻነት እየከወነ ነው አሉ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፤
ዋና ኮሚሽነሩ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኮሚሽኑ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ እንዳይሳካ ለማድረግ የተነሱ የውስጥና የውጭ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሳይበገር እየሠራ ይገኛል፡፡
የሐሳብና የሎጂስቲክስ ጉዳዮችን በማንሳት የሚወተውቱ የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖን በመመከት ራሱን ችሎ ሥራውን እያከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመጥቀስ “ምክክሩ የሚደረግበት ጊዜ አሁን አይደለም” የሚሉ ሙግቶችን ውድቅ በማድረግ ሂደቱን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።
በማንኛውም ሀገራዊ ምክክር ውስጥ ጣልቃ ገብነት ያለባቸው ሂደቶች እንዳልሰመሩ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ትልቅ ትምህርት መወሰዱንና ለዚህም ሲባል የኮሚሽኑን ነፃነት፣ ገለልተኝነትና አሳታፊነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አፅንኦት ሰጥተዋል።
አንዳንዶች ሀገራዊ ምክክሩ በግጭት ውስጥ ሆኖ መደረጉን እንደሚተቹ አንስተው÷ ምክክር በግጭት ውስጥም ጭምር የሚደረግ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት መርህ ሳይወጣ ነፃነቱን አስከብሮ እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ÷ ይህ ታሪካዊ ሂደት የሀገሪቱን ዘላቂ መረጋጋት ለመመለስና መጪውን ሀገራዊ ጉባኤ በስኬት ለመወጣት ትልቅ መሰረት እየጣለ መሆኑን አብራርተዋል።
በቅድስት ዘውዱ
መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ 👇