Fana: At a Speed of Life!

መከባበርና የጋራ ጥቅምን መርህ ያደረገው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የነጻነት፣ የሉዓላዊነት እና የፓን-አፍሪካኒዝም ተምሳሌት በመሆን የጀመረችውን ታሪካዊ ሚና፣ ዛሬ ላይ ተለዋዋጭ እና ሁሉን አቀፍ በሆነ የትብብር ዲፕሎማሲ በማበልጸግ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና ተደማጭነት ይበልጥ እያጠናከረች ትገኛለች።

የጋራ ተጠቃሚነትን፣ መከባበርን እና ቀጣናዊ ትስስርን ያማከለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ከፍ እንዲል ከማድረግ ባሻገር በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የትብብር መስኮች ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው።

ኢትዮጵያ ከአጋሮቿ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች በተመሳሳይ ጊዜ ከአዳዲስ አጋር ሀገራት ጋርም ሰፊ ትብብር በመፍጠር የዲፕሎማሲ አድማሷን የማስፋት ሥራዎችን እያከናወነች ሲሆን÷ በተለይም ከአፍሪካ፣ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከአውሮፓ ሀገራት እና ከአሜሪካ ጋር የተጠናከረ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትብብር መገንባቷ የዚህ አካሄድ አንዱ መገለጫ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ገንብታ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ እና በትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች በማገናኘት የምታደርገው ጥረት የቀጣናው የኢኮኖሚ ምሰሶነቷን አሳይቷል።

በዓለም አቀፍ መድረኮች የምታሳየው ንቁ ተሳትፎ በተለይም የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ባለብዙ ወገን መድረኮች ውስጥ በምታቀርባቸው ሀሳቦች የኢትዮጵያ ተደማጭነት ከፍ እንዲል ያደረገው ሌላ ጉዳይ ነው።

እንዲሁም የአፍሪካን ድምፅ በማጉላት እና የጋራ ችግሮችን በትብብር እንዲፈቱ በመደገፍ አሕጉራዊ ምልክት በመሆን እያከናወነች ያለችው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መዲና ብቻ ሳትሆን በአሕጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ያላት ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለች።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የንግድ ትስስርን ለማስፋት፣ የቱሪዝም ዘርፉን ለማጠናከር እና የልማት አጋርነቶችን ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች ቀላል የማይባል ውጤት የመጣባቸው ሲሆን÷ ይህም በኢንዱስትሪ፣ በኃይል፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች አዳዲስ የትብብር እድሎችን ፈጥሯል።

ኢትዮጵያ በትብብር፣ በመከባበር እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እሳቤ በመከተል እያጠናከረች የምትገኘው ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲ በአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ከፍ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ስም በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲቀጥል ያደረገው ታሪካዊ ክብሯ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ እየተከተለችው ያለው ንቁ፣ ሚዛናዊ እና ዘመናዊ የትብብር ዲፕሎማሲ ነው።

አሁን ላይ የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር እያከናወነቻቸው የሚገኙ የባሕር በር አማራጮችን የማስፋት እና የቀጣናዊ ትስስር ስትራቴጂዎች የዲፕሎማሲው ዋነኛ ትኩረት ሆነው ቀጥለዋል።

በመሆኑም የሀገር ውስጥ አንድነትን በማጠናከር እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን እና ሀገራዊ አጀንዳዎችን ወደፊት በማስቀጠል የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ተደማጭነት እና የላቀ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ እንዲጎለብት ሁሉም የበኩሉን ሊያበረክት ይገባል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.