Fana: At a Speed of Life!

የአገልግሎት አሰጣጥ ባሕል ለውጥ በመሶብ አንድ ማዕከል…

ባሕል የአንድ ማኅበረሰብ፣ የድርጅት ወይም የሕዝብ የጋራ መገለጫ የሆነና በጥልቅ ሥር የሰደደ የአስተሳሰብ፣ የእሴት፣ የእምነት፣ የልማድና የባሕርይ ድምር ውጤት ነው።

የአገልግሎት ዘርፍ ባሕል ተቋማትና ሰራተኞቻቸው ከተገልጋዮች ጋር የሚገናኙበት እና ሥራዎችን የሚያከናውኑበት ያልተጻፉ ግን በተግባር የሚታዩ ልማዶችን የሚያካትት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮች ይስተዋላሉ።

ይህ የአገልግሎት አሰጣጥ ባሕል የዜጎችን እንግልት ማብዛቱ ብቻ ሳይሆን፤ በሀገር ልማት እና በሕዝብ አመኔታ ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ይህን የቆየ የአገልግሎት አሰጣጥ ባህል በመሠረታዊነት ለመቀየር እየሰራ ይገኛል።

የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር አቀናጅቶ የያዘው መሶብ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ባለፈ፣ በመንግሥት ሠራተኛና በተገልጋዩ መካከል የነበረውን የግንኙነት ባሕል ቀይሯል፡፡

ቀደም ሲል አንድ ሰው ማንኛውንም ዓይነት አገልግሎት ለማግኘት ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን እንዲጨርስ የሚያስገድድ አሰልቺ አሰራር የነበረ ሲሆን ይህም ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር ዋነኛ በር ከፋች ሆኖ ቆይቷል።

አሁን በመሶብ ማዕከል አገልግሎቶችን የሚሰጡ የፌደራል እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት በአንድ ዲጂታል ሥርዓት ተቀናጅተው ዜጎች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ እያስቻለ ይገኛል።

ተቋማት ተቀናጅተው በአንድነት የሚሰሩበትን አዲስ የቅንጅት ባህል በመፍጠር በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ውስጥ ትልቁ ክፍተት ሆኖ የዘለቀውን ይህንን ባሕል ለመቀየር ወጣቶችንና ባለሙያዎችን በልዩ ሁኔታ አሰልጥኖ ወደ ሥራ አስገብቷል።

በማዕከሉ የሚሰጡት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፉ በመሆናቸው የአገልግሎት አሰጣጡን የተቀላጠፈ አድርጎታል፡፡

ዜጎች በዲጂታል ሥርዓት ተራቸውን ጠብቀው የሚስተናገዱበት ሁኔታ የተፈጠረ ሲሆን ይህ ለውጥ የመንግሥት አገልግሎት የዜጎች መብት እንጂ የኃላፊዎች በጎ ፈቃድ አለመሆኑን በተግባር ያሳየ ነው።

በዚህ መልኩ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ በታማኝነት፣ በቅልጥፍና፣ በግልጽነትና በዲጂታል አሰራር ላይ የተመሰረተ አዲስ የአገልግሎት ባሕል እየገነባ ነው።

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ አሁን ወደ ተለያዩ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች እየተስፋፋ መጥቷል፡፡

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥር ነቀል የሆነ የአገልግሎት ባሕል ለውጥ ለማምጣት ትልቅ መሠረት ጥሏል።

ይህም የመንግሥትን አገልግሎት ለዜጎች ቀላል በማድረግ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.