Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራ ትኩረት መስጠት ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራ ትኩረት መስጠት ይገባል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ፣ 2ኛ እና 3ኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን ከ1 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ዘላቂ ልማትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ለዕውቀት፣ ለምርምር፣ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግሥት ያስቀመጠውን የልማት አቅጣጫ ለማሳካት በቀረጸው የትምህርት ፖሊሲ በመታገዝ ብቃት ያለው፣ የፈጠራ ክህሎት የተላበሰና ምርታማ የሰው ኃይል ለመገንባት በትጋት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች ትውልድን በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥነ ምግባር በማነጽ ለሀገራዊ፣ አኅጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፍ ሁለንተናዊ ዕድገት እና ልማት የሚያበረክቱ ባለሙያዎችን በማፍራት ወሳኝ ሚና አላቸው ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በፈጣን ግሥጋሤ ላይ እንደሆነች እና ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞዋን የምታፋጥንበትን “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ራዕይ ቀርጻ ወደ ተግባር መግባቷን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ረገድ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ሥራ እንደሚጠበቅ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ለኢትዮጵያ ችግሮች ምላሽ የሚሰጥ ምርምር ማካሄድ፣ ቴክኖሎጂዎችን የማልማትና የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሥራ ፈጣሪዎችን የማፍራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳላባቸውም ጠቅሰዋል፡፡

በለይኩን አለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.