Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋት …

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፈር የወርቅ ያህል እንደሚከብር፣ በላብ የራሰ መሬትም መልሶ የላቀ ዋጋን እንደሚከፍል በተግባር ያሳዩ በሸካ ዞን የኪ ወረዳ አላሞ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወንድማማቾች፡፡

እነዚህ ወንድማማቾች ትናንት በፀሐይ ሀሩርና በድርቅ የሚታወቀውን የአላሞ በረሃ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ አንድ አካል የሆነችውን አላሞ ቀበሌ ዛሬ ወደ ለምለምነት ትቀየር ዘንድ ፈር ቀዳጅ ሆነው ታሪክ ሰርተዋል፡፡

የአካባቢያቸውን ስነ ምህዳር በመቀየርም ለአካባቢው አርሶ አደሮች ባለውለታ መበሆን ደረቅ እና የተራቆተ መሬት ዳግም ወደ ልምላሜ ተቀይሮ ፀጋ እንደሚሆን አሳይተዋል፡፡

ይንገስ ጌታቸው ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ የተመረቀ ሲሆን ተመርቆ ሲወጣ ከፊቱ ብዙ አማራጮች ቢኖሩትም የአርሶ አደር ቤተሰቦቹ ኋላ ቀር የሆነና የማይለወጥ አኗኗር ህሊናውን እረፍት ነሳው።

በትምህርት ያገኘውን እውቀት ተጠቅሞ የቤተሰቡን ህይወት ከመሰረቱ ለመለወጥ በመወሰን የተመረቀበትን የኢንጂነሪንግ ስራ ትቶ ወደ ግብርናው ዓለም ተቀላቅሏል፡፡

የግብርና ስራን የጀመረው ከቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ባገኘው የቫኔላ ችግኝ ነበር።

በርግጥ ወቅቱ የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባር መፋፋም የጀመረበት በመሆኑ እሱም ስለዚህ መሬት የነበረውን ሃሳብ እንዲያጠናክር አግዞታል።

ቫኔላን በማምረት የጀመረውን ስራ በማሳደግ ቡና፣ የቅመማቅመም ዝርያዎችንና ፍራፍሬዎችን ከሀገራዊው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ጋር በማስተሳሰር ወደ ላቀ ጥምር እርሻ ስራ መሸጋገር ችሏል፡፡

ታናሽ ወንድሙ ብርሃኑ ጌታቸው በቅጥር የሚሰራውን ስራ በመተው የወንድሙን ፈለግ ተከትሏል፡፡

ሁለቱ ወንድማማቾች በጥምር እርሻ ስልታቸው በዋናነት ቡናን ማዕከል በማድረግ ስራውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ጎን ለጎን እንደ ቫኔላ፣ ቁንዶ በርበሬ እና ካካዎ ያሉ ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ያላቸውን ቅመማቅመሞች በማልማት ላይ ይገኛሉ፡፡

በጥምር እርሻ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያና ሙዝ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎችን በብዛት ያመርታሉ፡፡

ይህ ትጋታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ላይ ወንድማማቾቹ ምርቶቻቸውን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ የላቀ ጥራት ያላቸውን ዘሮችና ችግኞችን በማዘጋጀት ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያከፋፈሉ ነው፡፡

ግብርና እውቀትና ትዕግስት ከተጨመረበት የማያልቅ ሀብት ነው የሚሉት ወንድማማቾቹ፤ አሁን ላይ ከዚህ ዘርፍ በዓመት እስከ 1 ሚሊየን ብር ገቢ በማግኘት ራሳቸውን በኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ መለወጥ ችለዋል።

ከዚህ ባለፈም የአካባቢውን አርሶ አደር ህይወት እና የአካባቢያቸው ስነ ምህዳር ለማሻሸል ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በደረቅነቱና በሀሩርነቱ የሚታወቀው ‘የአላሞ ቀበሌ’ ዛሬ መልኳ መቀየሩን የአካባቢው አርሶ አደሮች በአድናቆት ይመሰክራሉ።

እነሱ የተከሏቸውና ለአካባቢው ማህበረሰብ ያሰራጯቸው በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች ደርሰው አካባቢውን አረንጓዴ አድርገውታል፡፡

መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሰጠው ልዩ ትኩረት ለውጤታማነታቸው ትልቅ አቅም እንደሆናቸው ወንድማማቾቹ ይናገራሉ።

በተስፋየ ምሬሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.