Fana: At a Speed of Life!

በዓለም ዋንጫው የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ 3ኛ ጨዋታዎች ካናዳ ከስዊዘርላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ቫንኩቨር ከተማ ላይ አዘጋጇ ካናዳ ከስዊዘርላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚደረግ ሲሆን፤ ቡድኖቹ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ያጠናቀቁ ሲሆን በሁለተኛ ጨዋታቸው ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ በእኩል አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ምድቡን እየመሩ ይገኛሉ።
የጨዋታው አሸናፊ ምድቡን በቀዳሚነት በማጠናቀቅ ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላል።
ትልቅ የግብ ዕዳ ተሸክመው የምድቡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ኳታር እና ቦስኒያና ሄርዞጎቪና በተመሳሳይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምድብ ሦስት የመጨረሻ ጨዋታዎች፤ ብራዚል ከስኮትላንድ እንዲሁም ሞሮኮ ከሄይቲ በተመሳሳይ ሌሊት 7 ሰዓት ላይ ያጫወታሉ።
በዚህ ምድብ ብራዚል እና ሞሮኮ በአራት ነጥብ ሲመሩ ስኮትላንድ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ሄይቲ በምድቡ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለቱንም በመሸነፍ ከምድብ ማጣሪያው ውጪ ስትሆን፤ የዛሬውን ጨዋታ ለመርሐ ግብር ማሟያነት ታከናውናለች፡፡
በሌሎች መርሐ ግብር ደቡብ አፍሪካ ከደቡብ ኮሪያ እንዲሁም ቼክ ሪፐብሊክ ከሜክሲኮ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
የመጀመሪያ ሁለት የምድብ ጨዋታዎቿን ያሸነፈችው አዘጋጇ ሜክሲኮ ቀጣዩን ዙር መቀላቀሏን ያረጋግጣለች ሲሆን ደቡብ ኮሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ደቡብ አፍሪካ ዕጣ ፈንታቸውን ዛሬ ይለያሉ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.