Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኒውዚላንድ የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከኒውዚላንድ ጋር የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ፕሮቶኮል ከኒውዚላንድ ጋር ተፈራርማለች።

በጄኔቫ በሚገኘው የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው በዚህ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለምታደርገው ሒደት ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱን በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታትና በስዊዘርላንድ ያሉ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋብ ከበበው እና የኒውዚላንድ በዓለም የንግድ ድርጅት ቋሚ መልዕክተኛና የድርጅቱ አጠቃላይ ም/ቤት ሰብሳቢ አምባሳደር ክሌር ኬሊ ፈርመውታል።

አምባሳደር ፀጋብ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም ግልጽና በሕግ ላይ የተመሠረተ ሁለገብ የንግድ ሥርዓትን ለመደገፍ ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን በኢትዮጵያ እየተተገበረ ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ውስጥ ሀገራዊ ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሆኖ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

አምባሳደር ክሌር ኬሊ በበኩላቸው ለተመዘገበው ስኬት ደስታቸውን ገልጸው ፥ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን ኒውዚላንድ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.