Fana: At a Speed of Life!

የሚያስደንቅ ውበት የተጎናጸፈው የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ውበትና ድምቀት የሚያስደንቅ ነው አሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች።

የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በይፋ ተመርቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ባዘጋጀው የምስጋና መርሐ-ግብር ላይ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ፕሮጀክቱን ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ልማቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንና ለከተማዋ ውበት ተጨማሪ ድምቀት መፍጠሩን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ፈዲሉ ኢብራሂም÷ የቀበና ወንዝ ለረጅም ዘመናት በቆሻሻ መጣያነቱና በማይመች ሁኔታው ይታወቅ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የተከናወነው አስደናቂ የልማት ስራ ግን አካባቢውን በሚያስደንቅ ሁኔታ የቀየረው ሲሆን ይህም ትልቅ ደስታና እርካታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ስሙ በክፉ ይነሳ የነበረው ይህ አካባቢ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ውብ መልክዓ ምድርነት መቀየሩ እንዳስደነቃት የተናገረችው ደግሞ እስራኤል አሸናፊ ናት።

በአሁኑ ወቅት ስፍራው ለህጻናትና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ምቹ መጫወቻና የመዝናኛ ሆኖ መዘጋጀቱ እንዳስደሰታትም ተናግራለች።

ወጣት ዳንኤል በበኩሉ÷ የቀበና ወንዝ ዳርቻ ቀደም ሲል አስቀያሚና ለጤና ጠንቅ የነበረ ስፍራ መሆኑን አስታውሶ ይህን ስፍራ ውብ ያደረጉ አመራሮች ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ብሏል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ከድር ጃርሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ላይ የታየው ለውጥ እጅግ አስደናቂ እይታ መፍጠሩን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ይህ ስፍራ ቀደም ሲል በቆሻሻ ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በሐይቅ እና በአረንጓዴ ሥፍራ የተዋበ መሆኑንና አካባቢው ለኑሮ ምቹና ማራኪ ሆኖ መገንባቱን የጠቀሱት ደግሞ መቅደስ በቀለ ናቸው።

አካባቢውን ለረጅም ዓመታት የሚያውቁት አቶ አብደላ ኑሪ÷ ቀደም ሲል ስፍራው እጅግ ምቾት የማይሰጥና የሚያሳቅቅ ነበር፤በአሁኑ ወቅት የታየው ውበትና ልማት እጅግ አስገራሚ ነው፤ ተግባሩ ለመንግሥት ትልቅ ምስጋና የሚያሰጥ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.