ድንቅ የተፈጥሮ በረከት ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል የተገነባው ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ድንቅ ተፈጥሮ ከሰው ልጅ የማሰብ እና የመፍጠር አቅም ጋር ሲደመር እና ሲሰናሰል የሚገኘው ውጤት ማሳያ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለትውልድ ውጥን አካል የሆነው ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፤ ማህበረሰብን ለማበልጸግና ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአመራር ጥበብና ቁርጠኝነት ታይቶበታል።
‘ኒዒን ሌ ፓልም’ የተፈጥሮን ድንቅ መልክዓ ምድር የተወሰነ እሴት እና ፈጠራን በመደመር የሚገኝ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።
ሎጁ በ78 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ተፈጥሯዊ የፍል ውሃ መዋኛ፣ ሁለት ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቆች እና 3 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግር ጉዞ (ሀይኪንግ) መንገድን አካትቷል።
የሎጁ የማረፊያ ክፍሎች የግል መዋኛ ገንዳ ያላቸው ሁለት ፕሬዚዳንታዊ ቪላዎች 12 እርስ በርስ የተያያዙ የመኝታ ክፍሎች እና 16 ባለ አንድ መኝታ ቤቶችን ይዟል።
በተጨማሪም ዘመናዊ የምግብ አዳራሾች፣ የእንግዳ መቀበያ ህንፃ፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የቢሮ ክፍሎች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና ሁለት ሄሊኮፕተሮችን በአንድ ጊዜ ማሳረፍ የሚችል ስፍራ (ሄሊፓድ) ያካተቱ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታል።
ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ከቱሪስት መዳረሻነቱ ባለፈ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን በመሳብ ታላላቅ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ በቂ አቅም አለው።
የድንቅነሽ (ሉሲ) መገኛ እና የዳሎል የቱሪስት መዳረሻ በሆነው የአፋር ክልል መገንባቱ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የቱሪስት ቁጥር እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
በተጨማሪም ለአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ያለው ቅርበት የጎብኝዎችን ምቾት ከመጨመሩም በላይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የስራ ዕድልን የሚፈጥር ሲሆን፤ ይህም የክልሉን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግ በኩል ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ከሉሲ እስከ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፤ የአፋር ስጦታ ነው።
የ’’ገበታ ለትውልድ’’ ፕሮጀክት አካል የሆነው ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ የከባቢው ጸጋ የተገለጠበት ስራ መሆኑን በመግለጽ፤ ስራው የቱሪዝም ልህቀት እና የግብርና ዘርፍ መነቃቃትን አዲስ ምዕራፍ በማብሰር፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ የማድረግ ከፍተኛ ዐቅም አለው ነው ያሉት።
በአቤል ነዋይ