የመንገድ መሠረተ ልማት መስፋፋቱ የቱሪስት መዳረሻዎችን አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ያግዛል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ ዶርዜ ሎጅ ባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች መስፋፋታቸው በአካባቢዎቹ ያለውን አቅም አውጥቶ ለመጠቀም ያግዛል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የጫኖ-ጨንቻ መንገድ ፕሮጀክት የደረሰበትን ፈጣን የግንባታ ሂደት እንዲሁም የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻን ተመልክተናል ብለዋል፡፡
የ22 ኪ.ሜ የጫኖ-ጨንቻ መንገድና የ7 ኪሎ ሜትር የኤዞ-ጊርጫ ቅርንጫፍ መንገድን የያዘው የ29 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት በጥሩ አፈጻጸም ላይ መሆኑን ገልጸው፥ 13 ነጥብ 3 ኪ.ሜ ስራው ተጠናቅቋል ነው ያሉት።
የመንገዱ ስራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የማኅበረሰቡን ትስስር ይበልጥ ያጠናክራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ንግድና ጉዞን በማቀላጠፍ የአካባቢውን የኢኮኖሚ ልማት እንደሚያፋጥን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በማህበረሰቡ ጠንካራ መሪነት የተያዘውና የታደሰውን የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻ ጎብኝተናል ነው ያሉት።
በ40 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በቀዝቃዛና ሰንሰለታማ የተራራ ጋራ ላይ ያረፈው ይህ አስደናቂ ሥፍራ የአባያና ጫሞ ሐይቆችን እንዲሁም የእግዜር ድልድይ” ተብሎ የሚጠራውን የተፈጥሮ ድንቅ ዕይታ በአንድ ላይ በግልጽ የሚያሳይ ውብ ገጽታን ይሰጣል ብለዋል።
እንደ ዶርዜ ሎጅ ያሉ መሰል የቱሪስት መዳረሻዎች ጎን ለጎን የሚከናወነው የመንገድ መሠረተ ልማት መስፋፋት በስፍራው ያለውን እጅግ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የባህል አቅም ሙሉ በሙሉ አውጥቶ ለመጠቀም በእጅጉ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ዳያስፖራዎች እንዲሁም ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎች ይህንን አስደናቂ የተፈጥሮ ውበትና የበለጸገ የባህል ሐብት እንዲጎበኙና የታሪኩ ተጋሪ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።