የኢትዮጵያ ቱሪዝም እመርታ…
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ በማሳየት የሀገሪቱ ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር እየሆነ ይገኛል።
ይህም የሆነው የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ከነበረበት መዘናጋት በማውጣት የሀገሪቱን ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ እንዲሆን ስላደረገው ነው፡፡
መንግሥት ዘርፉን እንደ አንድ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ምሰሶና ሞተር አድርጎ በመቅረጽ፣ አዳዲስ ግዙፍ መዳረሻዎችን በመገንባት እና ነባር የባህል፣ የታሪክና የተፈጥሮ ፀጋዎችን በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
እሳቤው ካመጣቸው ትልልቅ ለውጦች አንዱ ቱሪዝምን ከተፈጥሮ ጥበቃ እና ከማህበረሰብ ልማት ጋር ያቀናጁ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መቅረጽና መተግበር ነው።
ይህም በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ ለሀገሪቱ ገቢና የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲስ ገጽታን የተላበሰ ሁለገብ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሆኗል። መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትና በፈጠረው አዲስ የቱሪዝም እሳቤ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ፀጋዎቻች ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየተሸጋገሩ ይገኛሉ።
ለዘርፉ እድገት መንግሥት በሰጠው ትኩረት አዳዲስ መዳረሻዎችና መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡
የመደመር መንግሥት አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከል ብቻ ሳትሆን ታላቅ የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ራዕይን ሰንቆ በመንቀሳቀስ ይህንኑ አሳክቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ከተሞች የተከናወኑት የኮሪደር ልማቶች የከተሞችን ውበት በማጎልበት፣ ለእግር ጉዞ እና ለብስክሌት ጉዞ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ቱሪዝሙን አነቃቅተዋል።
የዓለም ቅርስ የሆኑትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲለደስ ግንብ እና የጀጎል ግንብ የመሳሰሉ አንጋፋ ቅርሶችን በዘላቂነት የመጠበቅና የዕድሳት ሥራዎች ተከናውነዋል።
በቅርቡ የተገነቡት እና ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የአንድነት ፓርክ፣ የሸገር ፓርክ፣ የወዳጅነት ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የአብሬሆት ቤተ-መጽሐፍት፣ የዓድዋ ሙዚየም፣ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችና ፓርኮች፣ ወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ሪዞርት፣ ሃላላ ኬላ ሪዞርት፣ ጎርጎራ፣ ሎጎ ሀይቅ፣ ኮይሻ፣ የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት፣ የሀሮ ደንዲ ሎጅ፣ የሸበሌ ሪዞርት፣ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ የቱሪዝም መዳረሻ እና ሌሎችም በየአካባቢው በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የመደመር መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ትኩረት የተሰሩ ናቸው፡፡
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ባሉበት ሆነው በኢንተርኔት የኤሌክትሮኒክ ቪዛ በቀላሉ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
ይህም የጎብኚዎችን ፍሰት በእጅጉ አሳድጓል። በተጨማሪም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል የሚያልፉ መንገደኞች አዲስ አበባን እንዲጎበኙ የሚያስችለው የትራንዚት ቱሪዝም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ነው።
ከውጭ ጎብኚዎች ባለፈ፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ከፍተኛ እድገት እያሳየ ይገኛል። ዜጎች ሀገራቸውን እንዲያውቁና ውበቷን እንዲጎበኙ የሚያበረታቱ አደረጃጀቶች መፈጠራቸው፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እና የባህል ልውውጥን አጠናክሯል።
መንግሥት መዳረሻዎችን ከገነባ በኋላ ማስተዳደሩንና አገልግሎቱን ለግሉ ዘርፍ በሊዝ እና በሽርክና በማስረከብ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን አፋጥኗል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እመርታ የሀገሪቱን አወንታዊ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ረገድ የማይተካ ሚና አለው።
ይህ ዕድገት በዘላቂነት እንዲቀጥልና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዲጎለብት የቱሪዝም መዳረሻዎችን በዘመናዊ መንገድ የማልማትና አገልግሎቶችን የማዘመን ሥራዎችም እየተሰሩ ነው፡፡