Fana: At a Speed of Life!

የአካባቢ ጥበቃ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ብሔራዊ የደኅንነት ጉዳይ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአካባቢ ጥበቃ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ብሔራዊ የደኅንነት ጉዳይ ነው አሉ፡፡

3ኛው ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄዎች የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤና አሰራርን ማሻሻል ያስቻሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት የአፍሪካ ተምሳሌት እየሆነች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

የፕላስቲክ፣ የአደገኛ ቆሻሻና የድምፅ ብክለት ችግርን መፍታት የአካባቢ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ጤና፣ ኢኮኖሚ፣ ዘላቂ ልማትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ብሔራዊ የደኅንነት ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል

3ኛው ዙር ንቅናቄ ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ልማት የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ በሚለኩ ውጤቶችና በተጠያቂነት ላይ ማተኮር አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ከተሞችን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ የቱሪስት መስህብነታቸው እንዲያድግ ማስቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

የክልል መንግስታትና ከተማ አስተዳደሮች የሀገራዊ ንቅናቄውን ዓላማዎች ከአካባቢያቸው ሁኔታ ጋር በማጣጣም ግልጽ የክልልና የከተማ የትግበራ ዕቅዶችን ማዘጋጀትና በጀት መመደብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ለልጆቻችንና ለመጪው ትውልድ የምናስተላልፈው ትልቁ ቅርስ ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ ጤናማና ዘላቂ ኢትዮጵያ መሆን አለበት ብለዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.