Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በጽናትና ጀግንነት ግዳጁን የሚፈጽም ሠራዊት…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር በላቀ ቴክኖሎጂ የተገነባ ኃይል ነው አሉ፡፡

ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ እንዳሉት÷የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጀግኖችን አደራ በልኩ የሚፈጽም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲሟላ በጽናትና ጀግንነት ግዳጁን የሚያሳካ ጀግና ኃይል ነው።

ዘመናዊው ጦርነት ቴክኖሎጂንና ምርምርን ማዕከል አድርጎ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ጠቁመው÷ ሠራዊቱም ከዚህ የለውጥ ጉዞ ጋር አብሮ የሚራመድ፣ ኢትዮጵያን የሚመጥን እና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብር አቅም እየገነባ ነው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሚዲያ ባለሙያዎች በቅድሚያ ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ አቅም፣ አኩሪ ታሪክና በብዝሃነት የደመቀ፣ የለውጥና ዕድገት ኃይል የሆነ ጀግና ሕዝብ ባለቤት መሆኗን በትክክል መገንዘብ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

ወታደራዊ ጋዜጠኞች የሠራዊቱን ጀግንነት፣ የድል ታሪክና የከፈለውን አኩሪ መስዋዕትነት ለሕዝብ በማድረስ ረገድ የላቀ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ተቋማዊና ሀገራዊ ምርጥ ስኬቶችን ቀድሞ በማሳወቅ በተቋሙና በሠራዊቱ ላይ የሚነዙ አሉባልታዎችንና የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን መመከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሠራዊት የሚገነባው በሰላም ለመቆየት ሲባል ጦርነትን ለመከላከል መሆኑን ጠቅሰው÷ ካጋጠመ ደግሞ ሠራዊቱ በትንሽ መስዋዕትነት ድልን ለመቀዳጀት በሚያስችል አስተማማኝ የዝግጁነት አቅም ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የተገናዘበ የኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በመስራት የሠራዊቱን ሞራልና ሥነ ልቦና መገንባት እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታ ሒደት እንዲሳካ የሚዲያ ባለሙያዎች የሙያ ጀግንነትን በማረጋገጥ በዘርፉ ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ የመከላከያ ሚዲያና ኮሙኒዩኬሽን ማዕከል ከኃይሎች፣ ዋና መምሪያዎችና ከዕዞች ለተውጣጡ የሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች ባዘጋጀው ስልጠና የሠራዊት የግንባታ ስትራቴጂ ስልጠና ሰጥተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.