Fana: At a Speed of Life!

የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋት …

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለማችንን በአሁኑ ወቅት እየፈተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ጫናዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ ውሃን ጨምሮ ለተፈጥሮ ሃብት የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ ርምጃ በመውሰድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

ከእነዚህ ተግባራት መካከል ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟ በጉልህ እንዲጠቀስ አድርጓል።

በመንግሥት ቆራጥነት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያውያንን ልብና ጉልበት በአንድነት ያስተሳሰረ ታላቅ ሀገራዊ ተግባር ሆኖ ቀጥሏል።

ይህ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በይፋ የተጀመረው መርሐ ግብር ዛፍ ከመትከል ባሻገር ውሃን ጨምሮ ለተፈጥሮ ሀብቶች ዋስትና የሰጠ ውጤት አስመዝግቧል።

መንግሥት ለመርሐ ግብሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በባለቤትነት በመምራትና ህዝቡም ጥሪውን ተቀብሎ በነቂስ በመውጣት ላለፉት ዓመታት ያሳዩት ቁርጠኝነት የሀገሪቱን ደን ሽፋን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ብቻ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ ይህም ከቁጥር ባለፈ በተጨባጭ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለመጣው ለውጥ ማሳያ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ ይወድም የነበረው 72 ሺህ ሄክታር ደን ወደ 3 ሺህ ሄክታር ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

በወንዞች ላይ የሚፈጠረው ደለል እንዲቀንስ እና በወንዞች ላይ ይከማች የነበረው 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን ዓመታዊ የደለል ክምችት ወደ 208 ሚሊየን ቶን እንዲቀንስ በማድረግ ለውሃ ሀብት ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።

በተመሳሳይ መልኩ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ይደርስ የነበረው 130 ቶን ዓመታዊ የአፈር መሸርሸር አሁን ላይ ወደ 54 ቶን ዝቅ እንዲል በማስቻል ለምርታማነት እና ለአፈር ለምነት ትልቅ በረከት ሆኗል።

መርሐ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን፤ ለወጣቶችና ለሴቶች የገቢ ምንጭ በመሆን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዜጎች የአረንጓዴ ስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ችግኞችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ በቤተሰብ ደረጃ ተጨማሪ ገቢና የምግብ ምንጭ መሆን ችሏል።

አረንጓዴ ዐሻራ ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሞች በተጨማሪ ለዘላቂ የውሃ ሀብት ጥበቃ በርካታ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ደን ማልማት የዝናብ ውሃ ወደ መሬት ውስጥ እንዲሰርግ በማድረግ የውሃ ምንጮችን ያጠናክራል፣ የአፈር መሸርሸርን ይቀንሳል፣ የዛፍ ሥር አፈርን በማቆየት ወደ ውሃ አካላት የሚደርሰውን ደለል ይቀንሳል።

ደን ድንገተኛ ጎርፍን ስለሚቀንስ የውሃ አካላት በዘላቂነት ያገለግላሉ፤ ዝናብን በማመጣጠን የውሃ ሀብት ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ያግዛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.