በቡና ልማት ላይ የመጣው ለውጥ የአረንጓዴ ዐሻራን አስተዋጽኦ በተጨባጭ ያሳያል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቡና ልማት ላይ የመጣው ለውጥ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን አስተዋጽኦ በተጨባጭ ያሳያል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ለቡና ልማት የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን በዓለም ሶስተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር እንድትሆን አስችሏል።
የሪፎርም ስራው ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ስኬቶች ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማበርከቱን ጠቅሰው፤ የዘንድሮ የኢትዮጵያ የሸቀጦች ወጪ ንግድ 11 ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቡና ወጪ ንግድ ብቻ 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን አንስተው፤ ኢትዮጵያ የኮፊ አራቢካ መገኛ እንደመሆኗ በየትኛውም ዘመን ቡና ወደ ውጭ ስትልክ ብትቆይም ይህ ነው የሚባል ገቢ ማግኘት አልቻለችም ብለዋል።
በዚህም ሀገሪቱ ባለፉት 17 ዓመታት ከቡና ወጪ ንግድ ያገኘችው ገቢ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ብቻ መሆኑን አስታውሰዋል።
መንግሥት ለቡና ልማት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለቡና ምርት ዕድገት ስኬት አስተዋጽዎ ማበርከቱን አብራርተዋል።
ቡናን ካልተከልን፣ ካልተንከባከብን፣ ካልለቀምን፣ ካላጠብን፣ ካላሸግን እና ካላጓጓዝን ይህ ውጤት ሊመጣ አይችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ከመቻል አልፈን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የመጣው ለውጥ የሀገራዊ የሪፎርሙ ስኬት መገለጫ ነው ሲሉ አስረድተዋል።