Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ሕዝብ የጥቂት የወንጀለኞች ስብስብ ታጋች ሆኗል – አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ሕዝብ የጥፋት መረብ በዘረጉ የስልጣን ጥመኛ ጥቂት ወንጀለኞች ታጋች ሆኗል አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፡፡

በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሰላምና የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በህዝቡ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት አቶ ጌታቸው ረዳ ጠንካራ የስራ ባህል ያለው የትግራይ ሕዝብ በጥቂት የወንጀለኞች ስብስብ ምክንያት ከሀገሪቱ የልማት ተጠቃሚነት መገለሉን አንስተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያለውን ልማት የማደናቀፍ እንቅስቃሴ በማውገዝ የክልሉን ህልውና ማረጋገጥ ከፖለቲካዊ ልዩነቶች በላይ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ የጋራ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ አበረታች የልማት ስራዎች በትግራይ ክልል ለረጅም ጊዜ ተደራሽ ሳይሆኑ መቆየታቸው እንዳሳሰባቸው ገልጸው፥ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ለቀጣይ የልማት ስራዎች መሰረት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በትግራይ ክልል የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከተፈለገ መጀመሪያ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ክልሉን ለዓመታት በአፈና እና በወንጀል ተግባራት ውስጥ እያቆዩ የሚገኙ የጥፋት አባዜ የተጠናወታቸው ጥቂት የወንጀል አቀነባባሪዎች ምክንያት የህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት መና ሆኗል ነው ያሉት።

አሁንም ካለፈው ጥፋት መማር የማይፈልጉት እነዚህ አካላት በክልሉ ሰላምና ልማት እንዳይኖር የሚከተሉት አካሄድ ለክልሉ ህልውና ፈታኝ መሆኑን አንስተዋል።

መገናኛ ብዙሃን የክልሉን ሰላምና ልማት እንደ ቅንጦት ሳይሆን እንደ መሰረታዊ የህልውና ጥያቄ በመመልከት የጋራ አጀንዳ እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

በግዛቸው ግርማዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.