Fana: At a Speed of Life!

በጎነት ለማህበራዊ ትስስርና አብሮነት መጠናከር…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ልበ ቀናዎች ያለ ምንም ክፍያ ለሌሎች በመራራት ወይም ለማሕበረሰብ በመቆርቆር የሚያደርጉት መልካም ተግባር ነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት።

ይህ ተግባር “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር…” እንዲሉ ችግረኞችን ለመደገፍ፣ አደጋዎችን ለመከላከል፣ አብሮነትን ለማጠናከር እና በአስቸጋሪ ወቅቶች ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስችላል።

በዚህም ለተረጂው ወገን ብቻ ሳይሆን ለበጎ አድራጊውም ክህሎትን ለማዳበር፣ አዳዲስ ሰዎችን ለመተዋወቅ እና ከሁሉ በላይ የውስጥ ሰላምና እርካታን ለማግኘት ትልቅ እድል ይሰጣል። የመረዳዳት እና የመተሳሰብ ባህልን በማሳደግ የእርስ በርስ ትስስር ያጠናክራል።

በጎ ተግባር መልክ እና መገለጫው ብዙ ነው፤ የአዛውንቶችን መኖሪያ ቤት ማደስ፣ ሕጻናትን ወይም አቅም የሌላቸውን በነጻ ማስተማር፣ ደም መለገስ በየሆስፒታሎች ውስጥ ጠያቂና አስታማሚ የሌላቸውን ሕሙማን መርዳት፣ አካባቢን ማጽዳትና ማስዋብ ደጋግመን የምንሰማቸው ዘርፎች ናቸው።

የሕክምና፣ የሕግ፣ የቴክኖሎጂ ወይም ሌላ ዕውቀትን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በነጻ ማጋራትና ማማከርም እንዲሁ በዋጋ የማይተመኑ አበርክቶዎች ናቸው ።

ሰዎች ያለ ምንም ክፍያ ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን ለሌሎች ሲለግሱ፣ በማሕበረሰቡ መካከል ትስስርን እና አብሮነትን ለማጠናከር ትልቅ ድልድይ ይገነባሉ።

በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰዎችን ያለ ምንም የዘር፣ የሃይማኖት፣ የዕድሜ ወይም የኢኮኖሚ ደረጃ ልዩነት በአንድ ዓላማ ስር ያሰባስባል። እርስ በርሳቸው የመደማመጥ እና የመቀራረብ ዕድል ያገኛሉ። ይህ ደግሞ የተሳሳቱ ትርክቶችንና አመለካከቶችን እንዲሁም ጥርጣሬዎችን ያስወግዳል።

አንድ ሰው በሌላ ሰው ያለ ምንም ቁሳዊ ጥቅም ሲረዳ በማሕበረሰቡ ውስጥ ብቸኛ አይደለሁም የሚደርስልኝ ወገን አለ፤ የሚል የስነ-ልቦና ደህንነት ይፈጥራል። ይህ መረዳዳት በሰዎች መካከል ያለውን እርስ በርስ የመተማመን ስሜት ያሳድገዋል።

በጎ ፈቃደኝነት እኔ ምን አገባኝ ከሚል የግል ስሜት ወጥቶ ይህ የእኛ ጉዳይ ነው የሚል የባለቤትነት እና የጋራ ኃላፊነት ስሜትን ያጎለብታል።

በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የጋራ መገለጫ ነው። ከጥንት ጀምሮ ማሕበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና እርስ በርስ ለመረዳዳት የሚያገለግሉ በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉ።

ከአያት ቅድመ አያቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በክፉም በደግም ቀን፣ ሰዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት የቆየ ማህበራዊ ዋስትና አላቸው፡፡

እንደ እድርና እቁብ ባሉ የቁጠባ እና የአደጋ ጊዜ ምርኩዞች መደጋገፍ እንዲሁም በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በግብርና ሥራ ወይም በቤት ግንባታ ወቅት እጅ ለእጅ መያያዝ የነበረ አሁንም ያለ ኢትዮጵያዊ እሴት ነው፡፡

አሁን አሁን ይህ እሴት ከዘመናዊ እና ከተደራጁ አሰራሮች ጋር እየተቀናጀ ይገኛል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ ይበልጥ ተቋማዊ እየሆነ መጥቷል።

በርካታ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና የወጣት ማህበራት በተለያዩ ዘርፎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር እየሰሩ ይገኛሉ።

በየአመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች ሀይማኖት ብሔር ወይም ቋንቋ ሳይገድባቸው በመላ ሀገሪቱ ተዘዋውረው ወደ ሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ንቅናቄም አድጓል፡:፡

በዚህም የበጎ ፈቃድ ተግባር ሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድጋፍ ከመሆኑም በላይ፣ ከተለያዩ ብሔረሰቦችና አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች አብረው እንዲሰሩ በማድረግ ማህበራዊ አንድነትንና ሰላምን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በምህረት ደምሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.