የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ኢጋድ የቀጣናዊ የፀጥታ ትብብር ስትራቴጂያዊ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በቀጣናዊ የፀጥታ ትብብር ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስትራቴጂያዊ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተፈራርመውታል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ የኢትዮጵያ ፖሊስ በሪፎርም ያገኘውን አቅምና ተሞክሮ ለኢጋድ አባል ሀገራት ለማካፈል የሚያስችል ነው።
የስምምነቱ ዋና ዓላማ አንጋፋው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የህግ አስከባሪዎችን በስልጠና፣ በምርምርና በጋራ ጥናቶች በማብቃት የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህም ሁሉንም የአባል ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የትብብርና የማህበረሰብ ግንኙነት ማዕቀፍ ይፈጥራል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ሽብርተኝነትንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እያሳየ ያለውን ትልቅ ለውጥና ዕድገት በማድነቅ ስምምነቱ ለቀጣናዊ ውህደት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
ስምምነቱ የቀጣናውን የጸጥታ ኃይል ለማብቃት፣ የጋራ ስልጠናዎችን ለመስጠትና የመረጃ ልውውጥን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ታምራት ሙሉጌታ (ዶ/ር) ናቸው፡፡