አዲስ አስመጪዎችና ላኪዎች የብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥርን በአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲያገኙ ፍቃድ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ አስመጪዎችና ላኪዎች የብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥርን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የአንድ መስኮት አገልግሎት በኩል እንዲያገኙ ፍቃድ ሰጥቷል፡፡
ባንኩ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር አዲስ ፍቃድ ላወጡ አስመጪዎችና ላኪዎች የብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር አሰጣጥን የሚያቀል አዲስ የዲጂታል አገልግሎት አስተዋውቋል፡፡
አገልግሎቱ የባንኩ የሂሳብ ቁጥሮች በጉምሩክ ኮሚሽን አንድ መስኮት አገልግሎት በኩል ያለምንም ውጣ ውረድ እንዲሰጥ በማስቻል አስተዳደራዊ ሂደቶችን የሚቀንስና ፈጣን የንግድ አሰራርን የሚደግፍ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
አዲሱ አገልግሎት የሚመለከተው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ለሚያወጡና አዲስ ፍቃድ ላገኙ አስመጪዎችና ላኪዎች ብቻ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ያላቸው የንግድ ተቋማት ለሁሉም የገቢና የወጪንግድ ግብይቶቻቸው ይጠቀሙበት በነበረው ነባር ቁጥር መጠቀም እንደሚችሉ ባንኩ ገልጿል፡፡
ይህ አሰራር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከገቢና ወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ለማዘመን፣ የንግድ አሰራርን ምቹ ለማድረግ እንዲሁም የዲጂታል የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ጥረት አካል መሆኑንም አመልክቷል፡፡