የህልውና ጉዳይ!
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ህዝባዊ እና ህጋዊ ውክልና በሌለው ቡድን የባሕር በሯን አጥታለች። በዚህም ምክንያት ልማቷ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ማነቆ ከመሆኑ ባለፈ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸውን የብሔራዊ ደህንነቷን የተመለከቱ ዕቃዎችን ጨምሮ በጎረቤት ሀገር ወደብ ለማስገባትና ለማስወጣት ተገድዳ ቆይታለች።
የመደመር መንግሥት ካነሳቸው ቁልፍ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች አንዱ የባሕር በር ጥያቄ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ መንግሥት የባሕር በር ስትራቴጂን ወደ መድረክ አምጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ጉዳይ አስመልክተው ሲገልጹም፤ “እያደገ ለሚሄድ ሕዝብ የባህር በር ማግኘት ቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው” ብለዋል።
በዓለም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ኖሯት የባሕር በር ለሌላት እና ለወጪ ገቢ ምርቶቿ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ለምትከፍለው ኢትዮጵያ ጥያቄው ፈጣን ምላሽ ያስፈልገዋል።
እናም በሰላማዊ መንገድና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት የባህር በር ባለቤት ለመሆን ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እያካሄደች ትገኛለች።
ጥረቷም በታላላቅ የዓለም ሀገራት መሪዎች እና ተቋማት ድጋፍ አግኝቷል።
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ተገቢነት ያለው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግሥት የሚደግፈው መሆኑን አረጋግጠዋል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቱርክሜኒስታን በተካሄደው 3ኛው የተባበሩት መንግሥታት በማደግ ላይ ያሉ ወደብ አልባ ሀገራት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ወደብ አልባ ሀገራት የሚገጥማቸውን ተግዳሮት በመፍታት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ የራሷን ልማት ከማፋጠንና ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባሻገር ለቀጣናው ሀገራት መልከ ብዙ ፋይዳ አለው። ባለፈው ሚያዚያ ኢትዮጵያን የጎበኙት የአውሮፓ ፓርላማ አባል ቲየሪ ማሪያኒ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ፍትሃዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ሚናው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ ለቀጣናው ሀገራት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል። ቀይ ባሕር ከውድድር ይልቅ የትብብር ቀጣና እንዲሆን ከማስቻሉ ባሻገር፣ የባሕር ላይ ውንብድናን፣ ሽብርተኝነትን፣ የሕገወጥ የጦር መሣሪያ እና የሰዎች ዝውውርን የመሳሰሉ ድንበር ዘለል ችግሮችን በጋራ ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።
እንደ ሮበርት ኪዮሃኔ እና ጆሴፍ ናዬ ያሉ የዓለም አቀፍ ግንኙነት አጥኚዎች አስተያየት፤ ሀገራት በንግድ፣ በመሠረተ ልማትና በኢኮኖሚ በተሳሰሩ መጠን ከግጭት ይልቅ ትብብርን የመምረጥ ዕድላቸው ይጨምራል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ህጋዊ፣ ታሪካዊና በጋራ የመልማት ጥያቄ በመሆኑ ሁሉም ሊደግፈው ይገባል።
በቴዎድሮስ ሳህለ